በምዕራብ ሸዋ ዞን በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ8 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በፍራፍሬ እየለማ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሸዋ ዞን በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ8 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በፍራፍሬ እየለማ ነው
አምቦ፤ሐምሌ 9 /2018 (ኢዜአ)፦በምዕራብ ሸዋ ዞን በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 8 ሺህ 463 ሄክታር መሬት የሚሸፍን የፍራፍሬ ልማት እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በምዕራብ ሸዋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት የደን ልማት ባለሙያ አቶ ጉደታ ጡር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተያዘው ክረምት ከ15 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የፍራፍሬ ችግኞች ተዘጋጅተው እየተተከሉ ይገኛሉ።
የሚተከሉት የፍራፍሬ ችግኞች በአካባቢው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ማኅበረሰቡ ተጨማሪ ገቢ በማግኘት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን እንዲያሳድግ ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸውም ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩ ከተዘጋጁት የፍራፍሬ ዝርያዎች መካከል ፓፓያ፣ አቮካዶ፣ ሙዝ እና አፕል እንደሚገኙበትም ባለሙያው ጠቁመዋል።
በልማት ሥራው ዙሪያ ለአርሶ አደሮቹ ሥልጠና መሰጠቱን የጠቀሱት አቶ ጉደታ፤ በአሁኑ ወቅትም አስፈላጊው ሙያዊ ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በዞኑ በክረምቱ ወቅት በአጠቃላይ በ8 ሺህ 463 ሄክታር መሬት ላይ የፍራፍሬ ችግኝ ተከላ እየተካሄደ መሆኑንና በዚህ የልማት ሥራ ላይ 131 ሺህ 576 አርሶ አደሮች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።
በዞኑ የሚገኙ አርሶ አደሮች ከመደበኛ የግብርና ሥራቸው በተጓዳኝ በፍራፍሬ ልማት ላይ በመሰማራታቸው ተጨማሪ ገቢ ማግኘት መቻላቸውን ጠቅሰዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ባለፉት ዓመታት የተተከሉ የፍራፍሬ ችግኞች የአፈር መሸርሸርን ለመከላከልና የደረቁ ምንጮች እንዲያንሰራሩ በማድረጋቸው፣ የአርሶ አደሮቹን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አክለዋል።
በምዕራብ ሸዋ ዞን በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እስካሁን ከ11 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በፍራፍሬ ልማት መሸፈኑን ገልጸዋል።