ቀጥታ፡

በምስራቅ ቦረና ዞን የተሻሻለ የግብርና አሰራር ተግባራዊ መደረጉ ምርታማነትን ለማሳደግ እያገዘ ነው

ነገሌ ቦረና፤ሐምሌ 9 /2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ቦረና ዞን የተሻሻለ የግብርና አሰራር ተግባራዊ በመደረጉ ምርታማነትን ለማሳደግ እያገዘ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለጸ፡፡

በክልሉ በልግ አብቃይ ከሆኑ አካባቢዎች መካከል አንዱ የሆነው የምስራቅ ቦረና ዞን ከመጋቢት አጋማሽ እስከ ሚያዝያ የበልግ ዝናብና የዘር፣ ከሐምሌ እስከ ነሐሴ አጋማሽ ደግሞ የምርት መሰብሰቢያ ወቅት ነው፡፡

በጽሕፈት ቤቱ የአዝርእት ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ሊበን ቦሩ እንደገለጹት፤ በዞኑ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ከለማው ከ176 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ምርት እየተሰበሰበ ነው።


 

በዞኑ በበልግ አዝመራ ከለሙት የሰብል ዓይነቶች መካከል ስንዴ፣ ጤፍ፣ በቆሎና ቦለቄ ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

የበልግ አዝመራውን ምርታማነት ለማሳደግም ከ70 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉንም ገልጸዋል፡፡

በዞኑ የበልግ አዝመራ 162 ሺህ 804 ከፊል አርብቶ አደሮችና አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ጠቅሰው፣ ይህም የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ በበልግ አዝመራ ከለማው ሰብልም በ61 ሺህ ሄክታሩ በስንዴ ሰብል የለማ መሆኑንና ከዚህም መሬት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የስንዴ ልማቱን ለማሳደግ የትራክተር፣ የኩታ ገጠምና የመስመር አዘራር ዘዴ እንዲሁም ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ወጪና ጊዜ በመቆጠብ የምርት አሰባሰብ ሂደቱን ለማፋጠንም ኮምባይነሮች ሥራ ላይ መዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡


 

በዞኑ ሊበን ወረዳ የሜኤሳ ዳሎሬ ቀበሌ ነዋሪ አቶ በዳዳ ጀልዴሳ በአካባቢያቸው የሚስተዋለውን ዝናብ አጠር የአየር ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ እርጥበትን በመጠቀም በዘንድሮ በበልግ አዝመራ 3 ሄክታር መሬት ለመጀመሪያ ጊዜ በተሻሻለ የግብርና አሰራር የስንዴ ምርጥ ዘር ማልማታቸውን ገልጸዋል፡፡

መሬታቸውን በትራክተር አርሰው፣ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በመጠቀምና ሰብሉን በኮምባይነር እየሰበሰቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ አብጉዶ ዋሪዮ፤ በተሻሻለ የግብርና አሰራር ያለሙት ሰብል ውጤታማ እያደረጋቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

መንግስት ለስንዴ ሰብል ልማት የሰጠው ልዩ ትኩረት ለሥራቸው መሳካትና የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ እንዳገዛቸውም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም