ቀጥታ፡

በጅማ ዞን አዲሱ መናኸሪያ ለማሕበረሰቡ ምቹ አገልግሎት እየሰጠ ነው

 ጅማ፤ሐምሌ 9 /2018 (ኢዜአ)፦ በጅማ ዞን ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ዘመናዊ መናኸሪያ ለማሕበረሰቡ ምቹ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተገልጋዮች እና አሽከርካሪዎች ገለጹ።

አሽከርካሪዎች እና ተገልጋዮቹ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አዲሱ መናኸሪያ ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ የትራንስፖርት  መስተንግዶ ፣ ክፍተቶችንና መጨናነቅን  ያቃለለ ነው።

ከተገልጋዮቹ መካከል አቶ አብዱለዚዝ አላካ እና ሰሚራ አብዱልቃድር፤ አዲሱ መናኸሪያ ግልጽ፣ ምቹ እና ቁጥጥር የሚደረግበት አገልግሎት እንድናገኝ አድርጎናል ብለዋል።

የተሻሻለው አገልግሎት ምቹ የሆነ እና የተሻለ ጉዞ እንዲኖር  በማድረግ ትልቅ እፎይታን የሰጣቸው እንደሆነም ነው ያመለከቱት።


 

አቶ ነጋ ጀማል በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት በአዲሱ መናኸሪያ ምቹ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ከጅማ ወደ አዲስ አበባ የሚመላለሱት አሽከርካሪ ሙስሊም በድሩ  እና አብዱላሂ አባፊራ ፤ቀደም ሲል በነበረው  የተጨናነቀ እና አመቺ ያልሆነ መናኸሪያ በተደጋጋሚ ለአደጋ ይጋለጡ እንደነበር ገልፀዋል።

መናኸሪያው በአዲስ መልክ ተገንብቶ መጠናቀቁ ያለምንም ስጋትና እንግልት፣ ደህንነቱ የተጠበቀ ምቹ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።

በጅማ ዞን ትራንስፖርት ኤጀንሲ የስምሪት ኃላፊ የሺ ካሳ እንደገለጹት፤ በዞኑ ደረጃውን የጠበቀ የመናኸሪያ ማስፋፋያ በማካሄድ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የነበሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ ተችሏል።


 

ከዚህ ውስጥም ለተጓዦች በቴክኖሎጂ የታገዙ ምቹ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት መቻሉ በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመዘገብ ማድረጉን ገልጸዋል።

የትራንስፖርት አገልግሎትን ምቹ ለማድረግ መቻሉም በአካባቢው ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ በእጅጉ ለማነቃቃት እንዳስቻለም ነው የተናገሩት።

አዲሱ መነኸሪያ በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ከ1 ሺህ 100 በላይ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን ማስተናገዱን አመልክተው አፈፃፀሙ መናኸሪያው የነበረውን  የአገልግሎት አቅም እስከ አራት እጥፍ እንዳሳደገው ገልፀዋል።

ይኸም ማሕበረሰቡን ከተጨማሪ ወጪና እንግልት ከማዳኑም በላይ፣ ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ ህገ-ወጥ የትራንስፖርት ስምሪት እንቅስቃሴዎችን ለመታደግ ማስቻሉን ጠቁመዋል።

አዲሱ መናኸሪያ የጅማ ዞን ወረዳዎችን ጨምሮ እንደ ቦንጋ፣ ተርጫ፣ አመያ፣ ወልቂጤ፣ ቡኖ በደሌ እና ለሌሎችም አጎራባች አካባቢዎች ምቹና የተቀናጀ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ  ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም