ኢትዮጵያ፤ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የዕውቀት፣ የሰላምና የልማት ድልድይ!! - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ፤ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የዕውቀት፣ የሰላምና የልማት ድልድይ!!
ድንበር ያልገደበው ትስስር ኢትዮጵያ፤ የኢትዮጵያ ቀጣናዊ የዕውቀት፣ የሰላምና የልማት ድልድይ!!
በቤተልሔም ባህሩ
የሀገራት ድንበር በካርታ ላይ የተሳሉ መስመሮች ናቸው። በሰዎች ሕይወት ውስጥ ግን አንዳንድ ጊዜ ወንድማማችነትን የሚያሳድጉ ድልድዮች ይሆናሉ። በደቡብ ሱዳንና በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ያደገው ኒክሰን አንቶኒ ድንበርን የሚያውቀው እንደ መለያ መስመር ሳይሆን፣ እንደ መገናኛ መስመር ነው።
በልጅነቱም በድንበር አካባቢ ባሉ መንደሮች መካከል የሚኖረውን የገበያ ትስስር፣ የባህል መመሳሰል፣ የቋንቋ መቀራረብና ከሁሉም በላይ የሰዎች ተፈጥሯዊ መተማመን እየተመለከተ አድጓል። ስለዚህም ኢትዮጵያ በእርሱ አዕምሮ ውስጥ ከጎረቤት ሀገርነት ይልቅ የሁለተኛ ቤት ስሜት የፈጠረች ሀገር ሆናለች።
ጥቁር አንበሳ፤ ከሆስፒታል በላይ የቀጣናውና የአፍሪካ የእውቀት ማዕከል
ያ የልጅነት ትዝታ ግን አንድ ቀን የሕይወቱን መስመር የሚቀይስበት አጋጣሚ እንደሚፈጠር አላሰበም ነበር። ዛሬ ዶክተር ኒክሰን አንቶኒ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሕፃናት ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊቲ ትምህርቱን እየተከታተለ ይገኛል። በልጅነቱ በድንበር አካባቢ ያየው ወንድማማችነት ዛሬ ላይ በዕውቀትና በሕይወት ማዳን ሙያ እየታነጸ ይገኛል።
በልጅነቱ በድንበር ላይ የተመለከተው የሕዝቦች ወንድማማችነት ዛሬ በእጆቹ ውስጥ ሕይወትን የሚያድን ሙያ ሆኗል። ይህ የአንድ ሰው የሙያ ስኬት ብቻ አይደለም፤ ሀገራት በእምነት ሲተባበሩ የሚፈጠረው የሰው ታሪክ ነው። እዚህ ላይ ኢትዮጵያ የምትሰጠው ትምህርት ዲግሪ ብቻ አይደለም፤ ኃላፊነትም ጭምር ነው። ዛሬ በአዲስ አበባ የሚማረው ሐኪም ነገ በጁባ፣ በኪጋሊ ወይም በሞቃዲሾ ውስጥ የሺዎችን ሕይወት ሊታደግ ይችላል። ስለዚህ ዛሬ በክፍል ውስጥ የሚሰጥ አንድ ትምህርት ነገ በሌላ ሀገር የሚድን አንድ ሕፃን ሕይወት ሊሆን ይችላል። ይህም ነው በትብብር ላይ የተመሠረተ የሰው ኃይል ልማት የሚሰኘው ቃል፣ ከፖሊሲ ሰነድ ወጥቶ ሕይወት የሚያገኘው።
ነግቶ ሲጠባ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ኮሪደሮች ውስጥ ነጭ ጋውን የለበሱ ወጣት ሐኪሞች በፍጥነት ሲመላለሱ ይታያሉ። ከሩቅ ለሚመለከታቸው ሰው ማን ኢትዮጵያዊ፣ ማን ደቡብ ሱዳናዊ ወይም ማን ሩዋንዳዊ እንደሆነ መለየት ያዳግታል።
ሁሉም አንድ ቋንቋ ይናገራሉ—የሕክምናን።
ሁሉም አንድ ዓላማ አላቸው—ሕይወትን ማዳን።
ይህ ምስል ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና እየገነባች ያለውን አዲስ የትብብር ምዕራፍ በደማቅ ቀለም አጉልቶ ያሳያል። ዛሬ በኢትዮጵያ በሚገኙ 19 ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከ430 በላይ ከጎረቤት ሀገራት የመጡ ሐኪሞች በነፃ የስፔሻሊቲና የሰብ-ስፔሻሊቲ ስልጠና በመከታተል ላይ ናቸው። በዚህ መርሃ ግብር የተመረቁ 105 ሐኪሞችም ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ሕዝባቸውን እያገለገሉ ነው።
እነዚህ ቁጥሮች በራሳቸው ግን ሙሉ ታሪኩን አይነግሩም። ታሪኩ የሚጀምረው እንደ ኒክሰን ባሉ ወጣቶች ዐይን ውስጥ ከሚነበበው ተስፋ ነው። "ይህ ዕድል ለእኔ ትምህርት ብቻ አይደለም፤ ወደ ሀገሬ ተመልሼ ልጆችን የማድንበት ተልዕኮ ነው" ይላል። ያገኘው ልምድ የደቡብ ሱዳንን እንዲሁም የቀጣናውን አጠቃላይ የጤና ሥርዓት በጋራ ለማጠናከር እንደሚረዳ ያብራራል። ይህም የአንድ ወጣት ሐኪም ሃሳብ ብቻ አይደለም፤ የቀጣናው የጋራ የወደፊት ርዕይም ጭምር ነው።
የዶክተር ኒክሰን ታሪክ ብቻውን አይቆምም። በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መማሪያ ክፍሎችና በቀዶ ሕክምና ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ወጣት ሐኪሞች በየራሳቸው የተለያየ ታሪክ ቢኖራቸውም፣ የሚያገናኛቸው አንድ የጋራ ዕሴት አለ። እርሱም ኢትዮጵያ የዕውቀት ዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን ነው።
በአፍሪካ ታሪክ የሀገራት ግንኙነት ብዙ ጊዜ የሚገለጸው በፖለቲካ፣ በድንበር ወይም በደኅንነት መነፅር መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ያስረግጣሉ። ዛሬ ግን አዲስ ታሪክ በመፃፍ ላይ ይገኛል። የዚህ ታሪክ ቋንቋ የጦር መሣሪያ ሳይሆን የሕክምና አገልግሎት ነው፤ የጦር ሜዳ ሳይሆን የቀዶ ሕክምና ክፍል ነው፤ የፉክክር ምልክት ሳይሆን የጋራ ዕውቀት ነው።
ይህንን እውነታ የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ ደግሞ ደቡብ ሱዳናዊው ዶክተር ሲስቶ ዶሚኒክ ነው። በኢትዮጵያ የኦርቶፔዲክና ትራኦማ ቀዶ ሕክምና ስልጠና እየተከታተለ የሚገኘው ይህ ወጣት፣ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የተቀበለው የእንግዳ ተቀባይነት ባህል ከሙያው በላይ የሰው ልጅን ሰብዓዊ ክብር በጉልህ እንደሚያንጸባርቅ ይናገራል። "ሌሎች ሀገራት ሄጄ ተምሬያለሁ፤ ኢትዮጵያ ስመጣ ግን እንደ እንግዳ አልተሰማኝም። እንደ ቤቴ ነበር የተሰማኝ፤ እየኖርኩ ያለሁትም እንደዚያ ነው" የሚለው ንግግሩ ከአንድ ግለሰብ ልምድ በላይ ነው። ይህም የሀገራቱን ሕዝቦች ለዘመናት የተገነባ መተማመን የሚገጥ ማስረጃ ነው።
ዶክተር ሲስቶ ወደ ደቡብ ሱዳን ሲመለስ የሚያክመው የሀገሩን ዜጎች ብቻ አይሆንም፤ በዚያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም የእርሱ ታካሚዎች ይሆናሉ። በዚህ መልኩ በአንድ የቀዶ ሕክምና ክፍል የተገኘ ዕውቀት ድንበርን ተሻግሮ ሌላ ሀገር ውስጥ ሕይወት ያድናል። ይህ ደግሞ የዕውቀት ዲፕሎማሲ በተግባር ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ሕያው ምስል ነው።
ከኪጋሊ የተጀመረ ሕልም፤ በአዲስ አበባ የዘለቀ የመሻት ስኬት
የሩዋንዳዊው ዶክተር ሙሂር ፍራንክ ታሪክ ደግሞ ሌላ የቀጣናዊ ትብብር ገጽን ያሳያል። በኪጋሊ ሆስፒታሎች ውስጥ በትጋት የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ሐኪሞችን ሲመለከት ያደገው ይህ ወጣት፣ በፊታቸው ላይ ያየው ሙያዊ ብቃትና ርህራሄ አንድ ቀን እርሱንም ወደ አዲስ አበባ እንደሚያመጣው አስቦ አያውቅም።
ዛሬ ግን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኒውሮ ሰርጀሪ ስፔሻሊቲ ተማሪ ነው። ለእርሱ ኢትዮጵያ የትምህርት መዳረሻ ብቻ አይደለችም፤ በሩዋንዳ የሚያልመውን የጤና ሥርዓት የሚገነባበት ሁለተኛ ቤቱና የዕውቀት መሠረት ጭምር ነው። ሩዋንዳ በጤና ዘርፍ ያላትን የሰው ኃይል በፍጥነት ለማሳደግ በተያዘው ብሔራዊ ዕቅድ ውስጥ፣ በኢትዮጵያ የሚሰጠው ስልጠና የሚያበረክተው ሚና ትልቅ መሆኑን ይገልጻል።
እንደ ወጣቱ ዶክተር ገለፃም ''ይህ የሚያሳየው አንድ እውነት አለ፤ አንድ ሀገር የሌላውን ሀገር የሰው ኃይል ሲያጠናክር፣ በእውነቱ የጋራ የቀጣናውን መጪ ጊዜ እየገነባ መሆኑን ነው የሚያስገነዝበው'' ይላል።
በጤና ሚኒስቴር የጤና ዘርፍ ሰው ኃይል ልማት ማሻሻያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሰግድ ሳሙኤል በበኩላቸው፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት ሲሰጥ በቆየው ነፃ የሕክምና ስልጠና ዕድል እጅግ ውጤታማ እንደነበር ይገልጻሉ። ይህ ትብብርና አጋርነት በቀጣናው ሀገራት የሕክምና ዕውቀት እንዲጎለብትና የተሻለ የጤና ሥርዓት እንዲኖር ከማገዙም በላይ፣ በሀገራት መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር ድንበር ተሻጋሪ የጤና ችግሮችን በጋራ ለመለየትና ለመቆጣጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ያነሳሉ።
ዛሬ በነጭ ጋውን፤ ትናንት በሰማያዊ ቆብ
የዛሬውን ምስል ለመረዳት ወደ ትናንቱ መመለስ ያስፈልጋል። ዛሬ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ኮሪደሮች የሚታዩት ከደቡብ ሱዳንና ከሩዋንዳ የመጡ ወጣት ሐኪሞች ናቸው። ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ግን በእነዚያ ሀገራት የሚታዩት በሰማያዊ የተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበር መለያ ያሸበረቁ ኢትዮጵያውያን የሰላም አስከባሪዎች ነበሩ።
ዛሬ ግን ቦታው ተለውጧል፤ ዩኒፎርሙ ተለውጧል። ነገር ግን ተልዕኮው አልተለወጠም። ያኔ ሰላምን በማረጋጋት ሕይወትን ከጦርነት መታደግ ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ሕይወትን ከበሽታ የመፈወስ ተልዕኮ ነው። በዚህ መልኩ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላት ሚና ከአንድ መልክ ወደ ሌላ ቢሸጋገርም፣ መሠረታዊ ዓላማው ግን አልተቀየረም። ይህም ሰላምን መገንባት፣ ሰውን ማገልገልና ጎረቤቶችን ማጠናከር ሆኗል።
የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ታሪክ በ1950ዎቹ በኮሪያ በታዋቂው "ቃኘው ሻለቃ" የተጀመረ ሲሆን፣ በመቀጠል በኮንጎ፣ በላይቤሪያ፣ በቡሩንዲ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ድረስ የታሪክ ማህደር የተዘረጋ ነው። ይህም በታሪክ ድርሳናት መጻሕፍት ላይ የሚነበብ ብቻ አይደለም፤ ዛሬ በአዲስ አበባ በሚማሩ የአፍሪካ ወጣት ሐኪሞች ሕይወት ውስጥ በሕያው መልኩ ጎልቶ ይታያል።
ሩዋንዳ፤ የኢትዮጵያ የማይረሳ ውለታ
በ1994 ሩዋንዳ የተከሰተው የዘር ፍጅት በሰብዓዊነት ላይ የተቃጣ የአፍሪካና የዓለም ጥቁር ታሪክ ሆኖ ተመዝግቧል። በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ብዙዎች ሩዋንዳን በሩቅ ሆነው ሲመለከቱ፣ ኢትዮጵያ ግን ከሰላም አስከባሪዎቿ ጋር በመቆም የሰው ልጅ ሕይወት ከማንኛውም ጉዳይ እንደሚቀድም በተግባር አሳይታለች።
ይህን ታሪክ የሚያስታውሱት በኢትዮጵያና በጅቡቲ የሩዋንዳ አምባሳደር ቻርለስ ካሮምባ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፣ ''ሩዋንዳ በከባድ ፈተና ውስጥ በነበረችበት ወቅት ኢትዮጵያ ያደረገችልን ውለታ በሩዋንዳዊያን ልብ የታተመ፤ በሀገራቱ የግንኙነት ታሪክ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጭምር በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ ወታደራዊ ልዑክ አባልና ተሳታፊ ነበሩ፤ ይህ በሀገራቱ መካከል ያለው ጥብቅ ቁርኝት ማሳያ ነው።'' ስለዚህ ዛሬ አንድ ሩዋንዳዊ ወጣት በአዲስ አበባ ተምሮ ወደ ሀገሩ ሲመለስ፣ ያ ጉዞ በድንገት የተጀመረ አይደለም፤ ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት የተዘራ የመተማመን ፍሬ ዛሬ በዕውቀት እየጎመራ መሆኑን ነው።
ሀገራ አቋራጭ ወንዝ እንደ ደም ሥር፤ ኃይል እንደ አዲሱ የትስስር ቋንቋ
የሀገራት ጉርብትና በሰላም ማስከበርና ግጭት ማረጋገጥ በሚደረግ ትብብር ብቻ አይደለም፤ በሚጋሩት ዕውቀት፣ የተፈጥሮ ሀብትና በሚገነባ የጋራ ዕድገትም ጭምር ነው። ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ የቀጣናውን ግንኙነት ከፖለቲካ ግንኙነት መገለጫነት ወደ ተግባራዊ ትብብር ለመቀየር የቻለችባቸው መስኮች ብዙ ናቸው።
የኤሌክትሪክ ኃይልና የውሃ ሀብት ትብብርም ወሳኞቹ የመተሳሰሪያ ማዕከሎች ናቸው። ዛሬ ከኢትዮጵያ የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል የጅቡቲን ኢንዱስትሪዎች ያንቀሳቅሳል፤ በኬንያ የከተሞችን መብራት ያበራል፤ ወደ ሱዳንና ታንዛኒያ በማቅናትም የቀጣና ትስስር መስመር እየዘረጋ ነው። ይህም የኢትዮጵያ ዕይታ የእርስ በርስ መተማመንን የሚገነባ የሰላም መሠረት ነው።
ውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ደኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር ጥምረት ማዕቀፍ ውስጥ ቀጣናውን በኃይል የማስተሳሰር ታሪካዊ ሚናዋን ይበልጥ አጠናክራ ትቀጥላለች። የኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኃይል ትስስርም የጋራ ልማትን እያሳለጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል። አንድ ሀገር የጎረቤቷን ቤት የሚያበራ ኃይል ስታቀርብ፣ በተመሳሳይ ጊዜ የጋራ ዕጣ ፈንታንም እየገነባች መሆኑን ያመላክታል። ይህንን እውነታ የደቡብ ሱዳን የውሃና መስኖ ሚኒስትር ጀምስ ማዊች ሲገልጹት፤ ''ኢትዮጵያ የውሃና የኃይል ልማቷን የምታከናውነው ለራሷ ብቻ ሳይሆን የቀጣናውን የጋራ ተጠቃሚነት መርህ በማስቀደም ጭምር ነው።''
በተመሳሳይ አረንጓዴ አሻራን የመሳሰሉ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራሞች ከአንድ ሀገር ድንበር አልፈው ለመላው ዓለምና ቀጣናዊ የአየር ንብረት ደኅንነት ጉልህ ፋይዳ ያበረክታሉ። ወንዞች በሀገራት ካርታ ላይ ድንበር አያውቁም፤ የአየር ንብረትም ፓስፖርት አይጠይቅም። ስለዚህ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ትብብር ትዕምርትና የጋራ ህልውና ጉዳይ ነው።
የኢኮኖሚ ትስስር፤ የአዲሱ ዓለም የዕድገት ምኅዋር
እንደ ዶክተር ኒክሰን ያሉ ወጣቶች የኢትዮጵያን ታሪክ በሆስፒታል ውስጥ እየኖሩ ሲሆን፣ የቀጣናው የወደፊት ታሪክ ደግሞ በንግድ፣ በመጓጓዣና በኢኮኖሚ ትስስር እየተገነባ ነው። የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት በቅድሚያ ለጎረቤት መርህ የተቃኘ መሆኑ የሚታየው በዲፕሎማሲ መድረኮች ብቻ አይደለም።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የንግድ መድረክ ላይ የረጅም ዘመን የታሪክ ባለቤትና ከበርካታ ሀገራት ጋር የቆየ የንግድ ትስስር ያላት ሀገር ናት። ይህንን የንግድ ዲፕሎማሲዋን ይበልጥ ለማዘመንና ለማስፋፋት በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ብሪክስ (BRICS) ባሉ ጥምረቶች በንቃት በመሳተፍ ላይ ናት።
የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባል ለመሆንም የጀመረችውን የድርድርና የዝግጅት ጉዞ በቁርጠኝነት እያስቀጠለች ትገኛለች። በአህጉር ደረጃም ቀድሞ በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ)፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) አማካኝነት ቀጣናዊና አህጉራዊ የኢኮኖሚ ትስስሯን በማጠናከር የአፍሪካን የጋራ ገበያ ዕውን ለማድረግ እየተጋች ነው።
ይህ አጠቃላይ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ የንግድ ስትራቴጂ ነው። ለዚህ ማሳያም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀን ሶስት ጊዜ ወደ ሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ የሚያደርጋቸው የቀጥታ በረራዎች፣ የቀጣናውን የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርና የንግድ ፍሰት እጅግ እያቀላጠፉት መሆኑ ነው።
በአሁኑ ወቅት የሁለቱ ሀገራት የንግድ ሚዛን ተመጣጣኝ ደረጃ ላይ ነው። ሩዋንዳ ወደ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ገደማ የሚጠጋ ምርት ከኢትዮጵያ ስታስገባ፣ በምላሹ ደግሞ ስድስት ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ምርቷን ወደ ኢትዮጵያ ትልካለች። ወደ 40 የሚጠጉ የኢትዮጵያውያን ኩባንያዎች በሩዋንዳ ውስጥ በንግድና ልማት ሥራዎች ተሰማርተዋል። እነዚህ ኩባንያዎች በአጠቃላይ ከ73 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ካፒታል ይዘው መንቀሳቀሳቸው፣ ትስስሩ ከቀላል የንግድ ግንኙነት አልፎ የሀገራቱ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ሕይወት ወደ ማስተሳሰር ደረጃ መሸጋገሩን የሚያሳይ መሆኑን አምባሳደር ቻርለስ ካሮምባ ይገልጻሉ።
መደምደሚያ፡ የድንበር ልጅ... የአፍሪካ ተስፋ
ትናንት የኢትዮጵያ ወታደሮችና የሰላም አስከባሪዎች የቀጣናውን ሀገራት ሰላም ለመጠበቅ ኪጋሊና ጁባ ዘምተዋል። ከዓመታት በፊት በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ አንድ ሕፃን ልጅ ጎረቤቶች በፍቅር ሲኖሩ ይመለከት ነበር። ዛሬ ያ ሕፃን በአዲስ አበባ ሕይወት የሚያድን ዶክተር ሆኗል። ነገ ደግሞ ወደ ሀገሩ ተመልሶ የሚያክማቸው ሕፃናት የሚያገኙት ሕክምና፣ በኢትዮጵያ የተቀሰመ ዕውቀት ይሆናል።
ምናልባት የዚህ ታሪክ ትልቁ ትምህርት ይሄ ይሆናል። ሀገራትን በጣም የሚያስተሳስራቸው ነገር ስምምነት ብቻ አይደለም፤ የአንዱ ሕዝብ ልጅ በሌላው ሕዝብ ልጅ ሕይወት ውስጥ የሚያሳርፈው አሻራ ነው። ዶክተር ኒክሰን፣ ዶክተር ሲስቶና ዶክተር ሙሂር የተማሩትም የሕክምና ትምህርት ብቻ አይደለም፤ ድንበርን በሰብዓዊነት መሻገር የሚቻልበትን የአፍሪካ አዲስ ትርክት እንጂ።
ስለዚህ ይህ የአንድ ወጣት ሐኪም ጉዞ ብቻ አይደለም፤ ይህ ከድንበር መንደር የተጀመረ፣ በጥቁር አንበሳ ነጥሮ የወጣና በአፍሪካ የወደፊት ተስፋ የሚያስቀጥል የጋራ ታሪክ ነው። ይህ የታሪክ፣ የደም፣ የጥበብ፣ የውኃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና የንግድ ትስስር የአፍሪካ ህብረት የሚያልማትን የበለጸገችና የተሳሰረች አፍሪካ በተግባር ለማየት እንደሚቻል የሚያመላክት ህያውና ተስፋ ሰጪ ምስክር ነው።