በክልሉ ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ ለልማትና ለመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ ለልማትና ለመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል
ቡታጅራ፤ ሐምሌ 9/2018 (ኢዜአ):-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ ለህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት የገቢ ዕቅድ ተግባቦት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በቡታጅራ ከተማ እያካሄደ ነው።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ የክልሉን ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብ የህዝብን የልማትና የመልካም እስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ፡፡
በክልሉ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የዘርፉ አመራር ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ጠቅሰዋል፡፡
የገቢ አሰባሰብ ስራውን በልዩ ድጋፍና ክትትል በመምራት በዘርፉ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን በማረም በክልሉን ፈጣን እድገት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ቀመሪያ ረሻድ በበኩላቸው ለክልሉ ህዝብ የልማት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ገቢን በአግባቡ የመሰብሰብ ስራው በልዩ በትኩረት እየተመራ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ኃላፊዋ ገለጻ በክልሉ በ2018 በጀት ዓመት ከመደበኛና ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት 27 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 26 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል።
ገቢው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ9 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ጠቅሰው ለግብር ከፋዩ ማህበረሰብ የተፈጠረው ግንዛቤ፣ የገቢ አሰባሰቡ ወጥ በመደረጉ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ ስራ መሰራቱ እና የድጋፍና ክትትል ስርዓት መጠናከሩ ለገቢው መጨመር አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በተጀመረው የ2019 በጀት ዓመት 35 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብ መታቀዱንና ይህንንም ለማሳካት የግብር ህጉን የማስከበር እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።