የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአፍሪካ ደረጃ በአርዓያነት የሚጠቀስ ተቋም ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአፍሪካ ደረጃ በአርዓያነት የሚጠቀስ ተቋም ነው
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 9/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአፍሪካ ደረጃ በአርዓያነት የሚጠቀስ ተቋም መሆኑን የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዣን ካሴያ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አክብሯል፡፡
የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዣን ካሴያ በዚሁ ጊዜ፣ ተቋሙ በአህጉር ደረጃ ሞዴል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ሰፊ የለውጥ ጉዞ በማድረግ በአፍሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ከሚታመኑባቸው የልህቀት ማዕከላት አንዱ መሆን ችሏል ብለዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ወረርሽኞችን አስቀድሞ በመከላከል እንዲሁም ሲከሰቱ በፍጥነት በመቆጣጠር ረገድ የገነባው አቅም ለሌሎች አፍሪካውያን አገራት ትልቅ አርአያ መሆኑን አድንቀዋል።
በአፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የነበራቸው አገራት በቁጥር 12 ብቻ የነበሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ወደ 40 ማደጋቸውን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፣ ለዚህ ዕድገት የኢትዮጵያ ተሞክሮ ትልቅ ሚና እንደነበረው ተናግረዋል።
አህጉሪቱ በቀጣይ የሕብረተሰብ ጤና ተቋማት ያላቸውን አገራት ቁጥር ወደ 50 ለማድረስ ግብ የጣለች ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በዚህ ሂደት ውስጥ እንደ ዋና ሞዴል እንደምታገለግል አስረድተዋል።
በአፍሪካ ጠንካራ የላቦራቶሪ ትስስር መኖር የሕብረተሰብ ጤና ሥራዎችን ለመከወን ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ ማዕከሉ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የላቦራቶሪ ትስስር መረብ ለመገንባት ሥራ መጀመሩን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያም የዚህ የሙከራ ትግበራ መነሻ ከሆኑት ቀዳሚ አገራት አንዷ መሆኗን ገልጸዋል።
የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በቅርበትና በተቀናጀ መልኩ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያውያንም በኢንስቲትዩቱ ባስመዘገበው ውጤትና በደረሰበት የልህቀት ደረጃ ሊኮሩ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡