ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጠንካራ የሕብረተሰብ ጤና ሥርዓትና የላብራቶሪ አቅም ገንብታለች- ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ካሶሎ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 9/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጠንካራ የሕብረተሰብ ጤና ሥርዓትና የላብራቶሪ አቅም የገነባች ሀገር መሆኗን በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ካሶሎ ገለፁ።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በተገኙበት የ100ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ይገኛል።


 

በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ካሶሎ በዚሁ ወቅት፥ ኢንስቲትዩቱ ባለፈው አንድ ክፍለ ዘመን በሕብረተሰብ ጤና ዘርፍ ላስመዘገባቸው ታላላቅ ስኬቶች አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን በሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች አስተዳደር ረገድ የዓለም ጤና ድርጅት የትብብር ማዕከል አድርጎ ለመሰየም የሚያስችል የድጋፍ ደብዳቤ በቅርቡ ለጤና ሚኒስቴር እንደሚላክም ይፋ አድርገዋል።

በተጨማሪም የኢንስቲትዩቱ የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ቡድን ዓለም አቀፍ የእውቅና ማረጋገጫ የማግኘት ሂደት የጀመረ ሲሆን ይህ ሂደት ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኘ የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ቡድን ያላት ሁለተኛዋ የአፍሪካ ሀገር ትሆናለች ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ የቅኝት፣የላብራቶሪ፣ ምርምር፣ የአደጋ ጊዜ ዝግጁነትና ምላሽ እንዲሁም በማስረጃ ላይ የተመሠረተ የፖሊሲ ቀረጻን በማቀናጀት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ሥርዓት መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ግንባር ቀደም እና ጠንካራ ከሆኑ የሕብረተሰብ ጤና ላብራቶሪ ሥርዓቶች አንዱን መገንባት ችላለች ብለዋል።

በቅርቡ የተከሰተውን የማርበርግ ወረርሽኝ በመከላከል ረገድ ኢትዮጵያ ፈጣንና ውጤታማ ምላሽ በመስጠት ወረርሽኙን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ችላለች ሲሉ ጠቅስዋል።

የኢንስቲትዩቱ የዳበረ ልምድና የባለሙያዎች ብቃት አሁን ላይ ከኢትዮጵያ አልፎ ለሌሎች ጎረቤት ሀገራት በቴክኒክ ትብብር፣ በላብራቶሪ አገልግሎትና በሕብረተሰብ ጤና አመራር ዘርፍ ከፍተኛ ድጋፍ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 11 ቀን 1947 የዓለም ጤና ድርጅት መስራች አባል በመሆን በይፋ የተቀላቀለች ሲሆን ባለፉት 79 ዓመታት ከድርጅቱ ጋር በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የጤና ሥርዓትን በመቅረጽ ረገድ ጉልህ ሚና ስትጫወት መቆየቷን አስታውሰዋል።

ከሁሉም ስኬቶች ጀርባ ያለው የኢትዮጵያ ትልቁ ሀብት ሕዝቧና በኤፒዲሚዮሎጂ፣ በላብራቶሪ ሳይንስና በአደጋ ጊዜ አስተዳደር ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ፣ አዳዲስና ዳግም የሚቀሰቀሱ በሽታዎች፣ የጸረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች መላመድ እና ሰብአዊ ቀውሶች የወደፊቱን የጤና ገጽታ እየቀየሩት መሆኑን ጠቅሰዋል።

እነዚህን ለመቋቋም እንደ ኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያሉ ተቋማትን ማጠናከር፣ ጠንካራ አጋርነት መፍጠርና የማይበገሩ የጤና ሥርዓቶችን መገንባት የግድ ይላል ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ኢንስቲትዩቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር፣ የዲጂታል ጤና ሥርዓትን ለማስፋፋትና ዓለም አቀፍ የጤና ደንቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም