ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎችን ጤንነት መጠበቅ የሀገር ልማት፣ የኢኮኖሚ ዕድገትና የብሔራዊ ደህንነት ዋነኛ መሰረት መሆኑን በጽኑ ያምናል-ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 9 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎችን ጤንነት መጠበቅ የሀገር ልማት፣ የኢኮኖሚ ዕድገትና የብሔራዊ ደህንነት ዋነኛ መሰረት መሆኑን በጽኑ ያምናል ሲሉ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በተገኙበት የ100ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አክብሯል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለዜጎች ጤንነትና ለሀገር ደህንነት ያለው ሚና ወሳኝ ነው፡፡

የኢንስቲትዩቱ የመቶ ዓመት ጉዞ ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ጤና የምታደርገው ጥረትና የጤና ሥርዓት ግንባታ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

የሀገር ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ደህንነት ከህብረተሰብ ጤና ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው ጠቅሰው፥ የኢትዮጵያና የሕዝቦቿ ጥንካሬ የወደፊት እርምጃዋ በዜጎቿ ጤና መጠበቅ ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል፡፡

በዚህ ሂደት የሕክምና ምርምር አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በተለይም የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ፈታኝ የሆኑ ዓለም አቀፋዊ የጤና ቀውሶችን፣ ወረርሽኞችንና የተላላፊ በሽታዎችን በመከላከል ረገድ ያሳየው አፈጻጸም የሚደነቅ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በተለይም እንደ ኮቪድ-19፣ ኤምፖክስ እና ማርበርግ ባሉ ወረርሽኞች ወቅት ኢንስቲትዩቱ ያሳየው ፈጣን ምላሽና ሳይንሳዊ አመራር ለሀገሪቱ ክብርን ያጎናጸፈ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎችን ጤንነት መጠበቅ የሀገር ልማት፣የኢኮኖሚ ዕድገትና የብሔራዊ ደህንነት ዋነኛ መሠረት መሆኑን በጽኑ ያምናል ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ታዬ።

መንግሥት ጠንካራ ተቋማትን የሀገር ግንባታ መሠረት አድርጎ እንደሚመለከት በማስታወስ፣ ለኢንስቲትዩቱ የመሠረተ ልማትና የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።

ኢንስቲትዩቱ ለወደፊቱ ይበልጥ ውጤታማና ተወዳዳሪ እንዲሆን መንግሥት አመቺ የፖሊሲ መደላድልን እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።

ባለፉት ስኬቶች ላይ በመመሥረት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን የመከላከልና ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅምን ማዘመን እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የበሽታዎችን ስርጭት አስቀድሞ መተንበይ የሚያስችል ፈጣንና ዘመናዊ መረጃ አያያዝና ትንተና ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

የኢንስቲትዩቱ መቶኛ ዓመት የምስረታ በዓል ያለፈውን የሚዘክርበት፣ የአሁኑን የሚያመሰግኑበትና ለወደፊቱ የላቀ ዕቅድ የሚያቅዱበት መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢንስቲትዩቱ የፅናት፣ የእድሜና የህልውና ሚስጥር የሚቀዳው ከሰራተኞቹና ከተመራማሪዎቹ ጥንካሬ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ መንግሥት ለኢንስቲትዩቱ ተልዕኮ መሳካት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም