ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በ100 ዓመታት ለዜጎች የጤና ጥበቃ ውጤታማ ዘመን የማይሽረው አሻራ አሳርፏል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለፉት 100 አመታት ለዜጎች ጤና ጥበቃ ውጤታማነት ዘመን የማይሽረው የጥናትና ምርምር አሻራ ማሳረፉን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ ገለጹ።

ኢንስቲትዩት የ100ኛ በዓሉን ከዛሬ ሐምሌ 9 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ መርሃ ግብሮች ያከብራል።


 

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ በተገኙበት፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ይገኛል።

በክብረ በዓሉ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡራቃ (ዶ/ር)፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባን ጨምሮ የአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢንስቲትዩቱ ባለፉት 100 ዓመታት ለኢትዮጵያ የሕዝብ ጤና ጥበቃና ደኅንነት ዘርፎች ውጤታማ ሳይንሳዊ የጥናትና ምርምር ተግባራትን በማከናወን፣ ዘመን የማይሽረው ታሪካዊ አሻራ አሳርፏል።

ኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና ስጋቶችን ቀድሞ በመለየትና ምርምር በማካሄድ፣ የተለያዩ ክትባቶችን በማምረት እንዲሁም ለጤና አደጋዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት ረገድ ውጤታማ ሲሆን መቆየቱን ገልጸዋል።

በሀገር አቀፍ የጤና ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀረጻ ላይ ሳይንሳዊ የጥናት ውጤቶችን እንደ ግብዓት በማቅረብ፣ የሚከሰቱ ወረርሽኞችን ቀድሞ በማወቅ፣ በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ጥራት ያለው የላብራቶሪ ምርመራ ሥርዓት በመዘርጋት እንዲሁም የሙያተኞችን አቅም በመገንባት ውጤታማ ተግባራትን እንዳከናወነ አንስተዋል። 

በአሁኑ ወቅትም ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ወረርሽኞችን አስቀድሞ የመተንበይና የመረጃ ፍሰትን የማዘመንና የማሳደግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም ኢንስቲትዩቱን በምሥራቅ አፍሪካ የሕዝብ ጤና ምርምርና ስልጠና ግንባር ቀደም ተቋም ለማድረግ ራዕይ ሰንቆ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ የ100ኛ ዓመት በዓሉን ከዛሬ ሐምሌ 9 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ መርሃ ግብሮች ያከብራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም