ቀጥታ፡

ትምህርት ቤቶችን በግብአት በማሟላት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተሰራ ነው

ደብረ ብርሃን፤ ሐምሌ 9/2018(ኢዜአ)፡-ትምህርት ቤቶችን በግብአት በማሟላት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዓለማየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት በክረምቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የመጪውን የትምህርት ዘመን በተሳካ ሁኔታ ለማስጀመር ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

በቅድመ ዝግጅት ስራዎችም የአዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች በማስገንባት፣ የማስፋፊያና የጥገና ተግባራትን በማከናወን የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁንም ከ10 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በአምስት ትምህርት ቤቶች 18 የመማሪያ ክፍሎች ግንባታና የጥገና ስራዎች ተካሂዷል ብለዋል።

ከዚህ ውስጥም በመድሃኔ አለም የ1ኛና መለስተኛ ትምህርት ቤት ውሰጥ ደረጃቸውን የጠበቁ ሶስት አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ መከናወኑን በማሳያነት አቅርበዋል። 

በተጨማሪም የተማሪዎች መቀመጫ ፣ ወንበር ፣ጠረጴዛና የጥቁር ሰሌዳን የማሟላትና የጥገና ስራን ጨምሮ የትምህርት ቤቶችን ግቢ ጽዱ፣ ውብና ማራኪ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።

በዚህም መጪው አዲሱን የትምህርት አጀመማር ስኬታማ በማድረግ ጥራትን ለማስጠበቅ እንደሚሰራ ጠቁመው መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑድርጅቶች የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል። 

የባሶ 1ኛ ደረጃና መለስተኛ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር መምህር ጎበዜ ንጉሴ በሰጡት አስተያየት በትምህርት ቤታቸው የመማሪያ ክፍሎች እድሳትና የግቢ ማስዋብ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ህፃናት ወደ ትምህርት ቤት ሲመጡ ምቹና የተሟላ የመማር መስተማር ስራ እንዲኖር የሚያደረግ ነው ሲሉ አመልክተዋል።

በከተማ አስተዳደሩ 57 የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ የመንግስት ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም