ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሀገር አልፎ የአህጉራችን ኩራት ነው- ዶክተር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሀገር አልፎ የአህጉራችን ኩራት ነው ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እየተከበረ ይገኛል።

በበዓሉ አከባበር ሥነ-ሥርዓት ላይ የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ እና የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዓለም አቀፍ የጤና ዘርፍ ተወካዮችና አጋር አካላት ተገኝተዋል፡፡


 

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፥ ኢንስቲትዩቱ ላለፉት አንድ መቶ ዓመታት በሀገሪቱ የጤና ታሪክ ውስጥ ጉልህና ታሪካዊ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።

በኢንስቲትዩቱ ውስጥ የሚገኙ ተመራማሪዎች፣ የቅኝት ባለሙያዎች፣ የመረጃ ተንታኞች፣ የአደጋ ምላሽ ሰጪዎች እና የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች የሚጫወቱትን የላቀ ሚና አድንቀዋል።

ተቋሙ ሀገሪቱ አስቸጋሪ የጤና ፈተናዎችን ባለፈችባቸው ወቅቶች ያሳየው ተጋድሎ ትልቅና የሚደነቅ እንደነበር አስታውቀዋል።

በተለይ በኮቪድ-19 እና በተለያዩ አስጊ ወረርሽኞች ወቅት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በቅርበት በመተባበር የሰራውን ውጤታማ ስራ አንስተዋል።

የላብራቶሪ ምርመራና የቅኝት ስራዎችን በበላይነት መምራቱን፣ እንዲሁም በሳይንሳዊ ትንተናዎች የታገዘ ፈጣን የድንገተኛ አደጋ ምላሽ በመስጠት ግንባር ቀደም ሚና መጫወቱን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አቅም በአሁኑ ወቅት ከሀገር ወሰን ማለፉን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ተቋሙ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ጭምር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ አህጉራዊ ኩራት መሆኑን አስገንዝበዋል።

መንግሥት የጤናውን ዘርፍ ፍትሐዊነት ለማረጋገጥና ጥራትን ለማሻሻል በዋናነት በርካታ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ከገጠር እስከ ከተማ የጤና አገልግሎቶችን ማስፋፋት፣የእናቶችንና ህጻናትን ጤና ማሻሻል እንዲሁም ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የሕዝቡን ተሳትፎ ማሳደግና ዜጎች በጤና ወጪ ምክንያት ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና እንዳይጋለጡ ለማድረግ የባለቤትነት ስሜት በመፍጠር የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድንን የማስፋፋት ሰፊ ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ዓለም አዲስና ውስብስብ የጤና ሥጋቶች እንዳሉባት እያየን ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ እነዚህን ውስብስብ ሥጋቶች ለመመከት አደጋን አስቀድሞ የሚለይ፣ በፍጥነት የሚያስጠነቅቅ፣ በሳይንስ የሚተነትንና በተቀናጀ መልኩ ምላሽ የሚሰጥ ጠንካራ ተቋማዊ አቅም መገንባት መሆኑን በአጽንኦት ተስጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮዎቹን በታማኝነትና በብቃት መወጣት እንዲችል ጤና ሚኒስቴር አስፈላጊውን የፖሊሲ፣ የአመራርና የአቅም ግንባታ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም