ከንጋት ሐይቅ ከ10 ሺህ 700 ቶን በላይ የዓሳ ምርት ተገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
ከንጋት ሐይቅ ከ10 ሺህ 700 ቶን በላይ የዓሳ ምርት ተገኝቷል
አሶሳ፤ ሐምሌ 9/2018 (ኢዜአ)፡- ከንጋት ሐይቅ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ10 ሺህ 700 ቶን በላይ የዓሳ ምርት መገኘቱን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ የተፈጠረው ግዙፍ ሰው ሰራሽ ሃይቅ (ንጋት ሃይቅ) የኤሌክትሪክ ሃይል ከማመንጨትና የቱሪስት መስህብ ከመሆን ባለፈ በዓሳ ምርት የስራ እድል መፍጠር ችሏል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጉባ ላይ የተንጣለለው የንጋት ሃይቅ ከ70 በላይ ደሴቶች ያሉት ሲሆን በአካባቢው ልዩ ድባብ በመፍጠር ተመራጭ የመዝናኛ ስፍራ የሚሆን ነው።
የንጋት ሃይቅ በተለይም ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና አካባቢው ነዋሪዎች ተጨማሪ የኢኮኖሚ መሰረቶችን ይዞ የመጣ አቅም ሆኗል።
የንጋት ሐይቅ የዓሣ ሃብት ልማት፣ የቱሪዝምና የውስጥ ለውስጥ የውሃ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዲሁም በአካባቢው አዲስ የሥነ-ምህዳርና የአየር ንብረት ሚዛን ለማስጠበቅ የሚያስችል ነው።
የክልሉ ግብርና ቢሮ የእንስሳት እና የዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ብርሃኑ ኢትቻ (ዶ/ር)፤ በንጋት ሐይቅ ዓሳ ማስገር ስራ 46 ማህበራት ተደራጅተው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከንጋት ሃይቅ ብቻ 1ዐ ሺህ 799 ቶን ዓሳ ማምረት መቻሉን ጠቅሰው በክልሉ የዓሳ ምርት እድገት ማሳያቱን ተናግረዋል።
የተገኘው ምርት ከ2017 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ መጨመሩን ገልጸው በቀጣይም ተጨማሪ ማህበራት ወደ ስራ የሚገቡ መሆኑን ጠቁመዋል።
በክልሉ ከንጋት ሀይቅ በተጨማሪ ከዳቡስ፣ ዲደሳ እና በለስ ወንዞች የዓሳ ምርት በብዛትና በጥራት መመረቱን አንስተው በተያዘው በጀት ዓመትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ከክልሉ የዓሳ ምርት ወደ አዲስ አበባ እና ሌሎችም ከተሞች ለገበያ በማቅረብ ሁነኛ የገቢ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን ዶ/ር ብርሃኑ ገልጸዋል።
የንጋት ሐይቅ በተለይም በዓሳ ምርት ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ዓሳ በማስገርና ለገበያ በማቅረብ በሚያገኙት ገቢ ከራሳቸው አልፈው ለቤተሰባቸው ጭምር መትረፋቸውን ገልጸዋል።