ቀጥታ፡

በምዕራብ ወለጋ ዞን በበጀት ዓመቱ ለ156 ሺህ ሰዎች ሥራ ተፈጥሯል

ጊምቢ፣ሐምሌ 9/2018 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ወለጋ ዞን በተጠናቀቀው በጀት አመት ለ156 ሺህ ዜጎች  የስራ ዕድል መፈጠሩን የዞኑ ሥራ ፈጠራና ክህሎት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ደረጀ ጉድና ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በበጀት አመቱ ስራ አጥ ወገኖችን በማህበር በማደራጀት ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል።
 
በዞኑ በ2018 በጀት ዓመት ለ108 ሺህ ስራ አጥ ወገኖች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ አፈፃሙን ከፍ በማድረግ ለ156 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ታጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል፡

በዞኑ  የስራ አጥነት ችግር ለማቃለል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት የተከናወኑ ተግባራት አፈፃፀሙን ለማሳደግ እንዳስቻሉ ነው የተናገሩት።

 የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወገኖች በግብርና፣ በንግድ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በእንስሳት ልማት፣በውበት ስራ እና በሌሎች ዘርፎች መሰማራታቸውን ነው የገለጹት።

የስራ እድል ለተመቻቸላቸው ዜጎች ከ1 ቢሊዮን ብር ብድር እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን  በተሰማሩበት መስክ ዉጤታማ እንዲሆኑም የድጋፍና የክትትል ስራ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።



 
ከስራ እድሉ ተጠቃሚዎች መካከል መፊዛ አብዲ ከሌሎች ጓደኞቿ ጋር በመሆን ዝሪያቸው የተሻሻሉ  በጎችን በማድለብ ስራ ላይ መሰማራታቸውን ነው የምትናገረው።

በተሰማሩበት መስክ  የተሰጣቸው ሥልጠና፣ ድጋፍ አና ክትትልም ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያደርግ በመሆኑ የተሻለ ስኬት ለማስመዝገብ  እየሰሩ መሆኑን ነው የገለፀችው።


 

በማኅበር ተደራጅተው የመሥሪያ ቦታና የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆን በዶሮ እርባታ ስራ ላይ መሰማራታቸውን  የገለፀው ወጣት እዮብ ቶለሳ  በዘርፉ ውጤታማ ስራዎችን እየሰራን ነው ብሏል።

በተለይም ከቅርብ አመታት ወዲህ በመንግስት ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ የልማት ኢንሼቲቮች ወጣቱ የስራ ዕድል ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም