በክልሉ ከተሞች መኖሪያ ቤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በመገንባት የዜጎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት የተቀናጀ ጥረት ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ከተሞች መኖሪያ ቤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በመገንባት የዜጎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት የተቀናጀ ጥረት ይደረጋል
ጎንደር፤ ሐምሌ 9/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በከተሞች መኖሪያ ቤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በመገንባት የዜጎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት የተቀናጀ ጥረት የሚደረግ መሆኑን የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ገለጸ።
በክልሉ በተለይም በከተሞች የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል የሚያስችል የተቀናጀ አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።
በዚህ የልማት ጥረት ውስጥ የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በጡብ ማምረት ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ ስልጠና በጎንደር ከተማ እየተሰጠ ይገኛል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ አማካሪ አቶ ሽቤ ክንዴ፤ ኮሌጆቹ ቴክኖሎጅን የመቅዳት፣ የማላመድና የመፍጠር አቅማቸውን በመጠቀም የቤት ግንባታ ፕሮጀክት እቅዱ እንዲሳካ መስራት አለባቸው ብለዋል።
በዘመናዊ መንገድ ጡብ በማምረት በከተሞች ደረጃቸውን የጠበቁ፣ ውብና ማራኪ ቤቶችን መገንባት አለብን ያሉት አቶ ሽቤ፤ ለዜህም ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ከፍተኛ ሚና እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
የዚህ ስልጠና ዋነኛ ዓላማም ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ለእቅዱ መሳካት የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ነው ብለዋል።
የስልጠናው ተሳታፊዎችም ለልማት ፕሮጀክቱ ስኬት የበኩላቸውን ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)፤ የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ቤቶችን ለመገንባት እቅድ መያዙን መግለፃቸው ይታወቃል።