የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም የተገቡ ቃሎች ወደ ተጨባጭ ተግባር መቀየር አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም የተገቡ ቃሎች ወደ ተጨባጭ ተግባር መቀየር አለባቸው
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 8/2018(ኢዜአ) ፦ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን አሉታዊ ተፅዕኖዎች ለመቋቋም የተገቡ ቃሎችን ወደ ተጨባጭ ተግባር መቀየር አስፈላጊ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቴዎስ ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ፕሬዚዳንት ዶክተር ጌዲዎን ጢሞቴዎስ ዛሬ ከኮፕ 21 ፕሬዚዳንት ከሆኑት ሎረን ፋቢየስ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱም ሎረን ፋቢየስ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ ታላቅ ስኬት የተመዘገበበትን የፓሪስ ስምምነት በማጽደቅ የተጠናቀቀውን ኮፕ 21ን የመሩበትን ልምድ አካፍለዋል።
በተጨማሪም ለኮፕ 32 በሚደረጉ ዝግጅቶች እንዲሁም ስኬታማ የኮፕ 32 ጉባኤን ለማካሄድ አስተዋጽኦ ሊኖራቸው በሚችሉ ጉዳዮችና ካለፉት የኮፕ ጉባኤዎች በተገኙ ትምህርቶችና ግንዛቤዎች ላይ የሁለቱ መሪዎች ውይይት ትኩረት አድርጓል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) የፓሪሱ ስምምነት ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት እርምጃዎች ያለውን ዘላቂ ጠቀሜታ ገልጸው፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን አሉታዊ ተፅዕኖዎች ለመቋቋም የተገቡ ቃሎችን ወደ ተጨባጭ ተግባር የመቀየርን አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ላይ እምነትን የሚያጠናክር፣ ግልጽ፣ አካታች እና በአባል ሀገራት የሚመራ የኮፕ 32 ሂደትን ለመተግበር ያላትን ቁርጠኝነትም በድጋሚ አረጋግጠዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም በይዘትና ድርድር፣ በሎጂስቲክስና ኦፕሬሽን፣ በአጋርነት እንዲሁም ሚዲያና ኮሙኒኬሽንን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች በዝግጅት ረገድ የተመዘገቡት ተጨባጭ እድገቶችን አሳይተዋል።