ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን የሚያጎለብቱ ተምሳሌታዊ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን የሚያጎለብቱ ተምሳሌታዊ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሚገኝ የፓርላማ መረጃ ደኅንነት ፎረም ተሳታፊ እና የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ አካውንታቢሊቲ ላብ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማክዶናልድ ሌዋኒካ ገለጹ።

ኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ አለመግባባቶችንና ልዩነቶችን ለመፍታት፣ እንዲሁም ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ሀገራዊ ምክክር እያካሄደች ትገኛለች። 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም ባለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እና በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

በዚህም መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ዛሬ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በይፋ ተጀምሯል።

የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ አካውንታቢሊቲ ላብ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማክዶናልድ ሌዋኒካ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ብሔራዊ መግባባትን የሚገነባ የዴሞክራሲ መንገድ ነው። 

አክለውም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመሠረታዊ ሀገራዊ ችግሮች ላይ ለመመካከርና መፍትሔ ለመስጠት በጉባኤው መሰባሰቡ ተምሳሌታዊ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት እና የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ወደ መካሄድ መሸጋገሩ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን የሚያጎለብቱ ወሳኝ እርምጃዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። 

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት፣ የበርካታ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውክልና ማግኘታቸው የዴሞክራሲ ባህልን ለማጎልበት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም