በሲዳማ ክልል የህዝብና የአመራር አቅምን በማቀናጀት የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ማሳካት ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የህዝብና የአመራር አቅምን በማቀናጀት የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ማሳካት ተችሏል
ሀዋሳ፤ ሐምሌ 8/2018 (ኢዜአ):-በሲዳማ ክልል የህዝብና የአመራር አቅምን በማቀናጀት የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ማሳካት መቻሉን የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሃም ማርሻሎ ገለጹ፡፡
''ከምርጫ ድል ማግስት ጠንካራ መንግስት'' በሚል መሪ ቃል የክልሉ የ2018 በጀት ዓመት የመንግስትና የፓርቲ ሥራዎች አፈጻጻምን የሚገመግም መድረክ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡
የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሃም ማርሻሎ በወቅቱ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ የአመራርና የህዝብ አቅምን በማቀናጀት የግብርና ምርትና ምርታማነትን የማሳደግና ኢንዱስትሪውን በተገቢው በመምራት የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር ተችሏል።
በተለይ የኑሮ ውድነትን ለማርገብ የግብርና ምርታማነትን ማሳደግን ጨምሮ ገበያ ተኮር ምርቶችን የማምረት ግብ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰው፣ በየደረጃው ያለው አመራር ተገቢውን ድጋፍ በማድረጉ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል፡፡
ውሃ አጠር በሆኑ አካባቢዎች በጉድጓድ ውሃ ማልማት መጀመሩና መሬት ጾም እንዳያድር መደረጉም ምርታማነት እንዲጨምር ማድረጉን አያይዘው ገልጸዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሳካትም ለክህሎት መር ስልጠና እንዲሁም የከተማና የገጠር የልማት አቅምችን ወደ ውጤት መቀየር ላይ በቅንጅት መሰራቱን አስረድተዋል።
የገጠርና የከተማ ኮሪደር ልማቶች ኢኮኖሚና ማህበራዊ ፋይዳቸውን ለማጉላትም ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ጠቅሰዋል።፡
መንግስታዊ አገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ ወደ ሥራ የገቡ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች ቀደም ሲል ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አስችሏል ብለዋል፡፡
በተከናወኑ ሥራዎች በሁሉም ዘርፍ የተመዘገበው ውጤት አመራሩ ተናቦ በቁርጠኝነት ከሰራ ያቀዱትን ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል።
በግምገማ መድረኩ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች የተገኙ ሲሆን የበጀት ዓመቱ የፓርቲና የመንግስት ዕቅድ አፈጻፀም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።