ቀጥታ፡

ብክለትን በመከላከል ጽዱ ኢትዮጵያን ለቀጣይ ትውልድ ለማውረስ የጋራ ጥረት ያስፈልጋል

ዲላ፤ ሐምሌ 8/2018 (ኢዜአ):-የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ጽዱ ኢትዮጵያን ለቀጣይ ትውልድ ለማውረስ የጋራ ጥረትን ማጠናከር እንደሚገባ የኢፌዴሪ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 3ኛው ዙር "የጽዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ" የአካባቢን ብክለት መከላከል ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በዲላ ከተማ ተካሂዷል።


 

ንቅናቄው ለቀጣይ ሦስት ወራት የሚተገበር ሲሆን የፕላስቲክና የድምፅ ብክለትን መከላከል እና የጎጂ ኬሚካል አጠቃቀምን መቀነስን ዓላማ ያደረገ ነው ተብሏል።

የኢፌዴሪ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያ በወቅቱ እንዳሉት የአካባቢ ብክለት በዜጎች የእለት ተዕለት ኑሮ ላይ ጫና እያሳደረ ነው።

በተለይ የፕላስቲክና የድምፅ ብክለት እንዲሁም ጎጂ የኬሚካል ቆሻሻ ተጽኖው ከፍተኛ መሆኑን አንስተው፣ የጽዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ ንቅናቄ የህብረተሰቡ ግንዛቤን በማሳደግ ችግሩን እያቀለለ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ የከተማና የገጠር የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ ልማትና የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የአካባቢ ብክለትን ከመከላከል ባለፈ ጽዱ ኢትዮጵያን ለመገንባት እያስቻሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ንቅናቄው ለቀጣይ ሦስት ወራት የሚተገበር ሲሆን የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማጠናከር እንዲሁም ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም ሀብት መፍጠርን ጨምሮ ተግባራዊ የመፍትሔ እርምጃዎች ይወሰዳሉ ብለዋል።

በዚህም የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ጽዱ ኢትዮጵያ ለቀጣይ ትውልድ ለማውረስ የጋራ ጥረትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ገልጸዋል።

ለቀጣይ ትውልድ ንጹህ እና ጤነኛ አካባቢን ለመፍጠር የጋራ ጥረትን ማስቀጠል እንደሚገባ ያነሱት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቴ ግጄ ናቸው።


 

በክልሉ የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ዘላቂ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተው ንቅናቄው የዚሁ አካል ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ ቆሻሻና ብክለትን በመጸየፍ ጽዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ ለማውረስ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝም ጥሪ አቅርበዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የዘርፉ አመራሮች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣  የሃይማኖት መሪዎች፣ ተማሪዎች እና ባለድርሻዎች ተገኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም