ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን አሸናፊ እናድርግ- እናት ሙዶ አኮ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2018 (ኢዜአ)፦ከደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር ወረዳ የካራ ማህበረሰብ ተወካይ እና የሰላም እናት ሙዶ አኮ በሀገራዊ የምክክር የመክፈቻ ጉባኤ ላይ  ኢትዮጵያን አሸናፊ እናድርግ ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት  በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተካሂዷል። 


 

በመክፈቻ ጉባኤው ከደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር ወረዳ የመጡት የካራ ማህበረሰብ ተወካይ እና የሰላም እናት ሙዶ አኮ፣ በዚሁ ወቅት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። 

እናት ሙዶ  የኢትዮጵያ ሴቶች እና እናቶች ለዘመናት በታሪክ ሂደት ውስጥ ተሳትፏቸው የነበረው በደልን በመቀበል እና ሀዘንን በመጋራት ብቻ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህም እናቶች ለዘመናት በሰላም እጦት የደረሰባቸውን መከራ በንግግራቸው ጠቅሰዋል።

ዛሬ ግን ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጻቸውን ለመስማት በመጥራቷ የኢትዮጵያ ሴቶችን ድምጽ በመወከል፣ ታሪካዊውን የምክክር መድረክ በክብር መቀላቀላቸውንም በደስታ ተናግረዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ ያላቸውን ተስፋ እና ሙሉ እምነት አንጸባርቀዋል። 

እናት ሙዶ አኮ፣ ሀገሪቱ ያሳለፈችው ፈታኝ ጊዜ የጋራ መግባባት በመጥፋቱ እንደሆነ በማሳየት ለነገ የምንተወው ተስፋ መሠረቱ የዛሬው መደማመጥ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ መኖሪያ እንደሆነች ያነሱት እናት ሙዶ፣ በልባችን የያዝነውን የቀድሞ ቁጣ እና የቂም ቋጠሮ በመፍታት፣ ተመካካሪዎች በሙሉ ለሀገራዊ ለውጥ በጋራ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል። 

ማን ያሸንፋል ከሚል አስተሳሰብ በመውጣትም፣ ኢትዮጵያን አሸናፊ በሚያደርግ የጋራ ዓላማ ዙሪያ መሰለፍ እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል።

የምክክር መድረኩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና ብልፅግና ቁልፍ ምዕራፍ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

በመድረኩ ኢትዮጵያን አሸናፊ እናድርግ ያሉት እናት ሙዶ፥ የነገዋን ብሩህ ኢትዮጵያ የመገንባት ትልቅ አደራችንን እንወጣ ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም