የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የአፍሪካ ቀንድን ወደ ብሩህ ተስፋ የሚመራ አይነተኛ እርምጃ ነው -የኢጋድ ዋና ፀሐፊ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የአፍሪካ ቀንድን ወደ ብሩህ ተስፋ የሚመራ አይነተኛ እርምጃ ነው -የኢጋድ ዋና ፀሐፊ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ መላውን የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ወደ ብሩህ ተስፋ የሚመራ አይነተኛ እርምጃ መሆኑን የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ዛሬ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት በዓለም ታሪክ ውስጥ በግጭት የተገነባም ሆነ ያተረፈ ሀገር አለመኖሩን በመጥቀስ፣ የኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት ሊረጋገጥ የሚችለው በሰላማዊ ውይይትና በመደማመጥ ብቻ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ማንነቷን የምትፈልግ አዲስ ሀገር ሳትሆን፣ ከጥንታዊና ጠንካራ ስልጣኔዎች አንዷ መሆኗን ጠቁመዋል።
በታሪካችን፣ በባህላችንና በእምነታችን ውስጥ በርካታ ባህላዊ የእርቅ ስርዓቶች ስላሉ፣ ኢትዮጵያ የራሷን ቁስል የምታክምበት ቁልፍ በእጇ ላይ መሆኑንና መፍትሔ ፍለጋ ወደ ውጭ ማማተር እንደማያስፈልጋት አጽንኦት ሰጥተዋል።
በፖለቲካዊ ሕይወት ውስጥ በአስተዳደር፣ በሀብት ክፍፍልና በውክልና ዙሪያ የተለያዩ አመለካከቶች መኖራቸው ሙሉ በሙሉ ተፈጥሯዊና የተለመደ ነው ብለዋል።
እነዚህን ልዩነቶች በኃይል ለመፍታት መሞከር ግን መሠረታዊ ስህተት መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እናቶች፣ አባቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ዛሬ የተወካዮቻቸውን መድረክ እየተመለከቱ ያሉት በጉጉትና በታላቅ ተስፋ እንደሆነ በማንሳት የግጭት አዙሪት በሀገሪቱ ማብቃት እንዳለበት ገልጸዋል።
ልዩነቶችን በውይይትና በጋራ መከባበር መፍታት እንደምንችል ለራሳችንና ለዓለም የምናስመሰክርበት መድረክ ነው ብለዋል።
የምክክር ጉባኤው ተሳታፊዎች ይህንን ታሪካዊ ዕድል በአግባቡ በመጠቀም በአስተውሎት እንዲመካከሩ በመጠቆም፥ ኢጋድ በዚህ አስደናቂና ታሪካዊ የሰላም ጉዞ ውስጥ ከኢትዮጵያ ጎን በጽናት እንደሚቆም አረጋግጠዋል።