ቀጥታ፡

በደብረ ብርሃን ከተማ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

ደብረ ብርሃን፣ ሐምሌ 8/ 2018 (ኢዜአ)፡-በደብረ ብርሃን ከተማ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱ ተገለፀ።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫ  ላይ ያተኮረ የምክከር መድረኩን አካሂዷል።


 

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ወርቃለማሁ ኮስትሬ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ከተማ አስተዳደሩ የጤና አገልግሎትን ተደራሽነት ለማሳደግና ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችል ድጋፍ እያደረገ ነው። 

ይህም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር አበረታች ውጤት እንዲመዘገብ ያደረገ ነው ብለዋል።

በቀጣይም በከተማዋ በንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም እየመጣ ያለውን እድገት የሚመጥን የጤና ስርአት ለመዘርጋት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

ለዚህም በከተማዋ የሚገኙ ጤና ተቋማትን በግብዓት፣ በሰው ሃይልና በሌሎች ቁሳቁሶች ለማሟላት በሚደረገው ጥረት ውስጥ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም ነው ያረጋገጡት።


 

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ በቀለ ገብሬ በበኩላቸው ፤የጤና ተቋማትን ደረጃ በማሻሻልና ተደራሽነትን በማስፋት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት አስገኝተዋል ብለዋል። 

ጥራቱን የጠበቀ የላብራቶሪ አገልግሎት በመስጠት፣ የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎትን በማሻሻል፣  በወሊድ አገልግሎት ጥራትና ሌሎች ዘርፎች አበረታች ውጤት መመዝገቡን ነው የተናገሩት። 

በአሁኑ ወቅት በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን 32 ሺህ 727 አባውራና እማውራዎችን በማቀፍ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

በቀጣይም የከተማዋን እድገት የሚመጥን የጤና ስርአት የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል  ብለዋል። 

በጤና ጣቢያ ደረጃ የቀዶ ህክምና ፣ የዲጅታላይዜሽን ስርአት፣ የተቋማት ጽዳት፣ ውበትና ሌሎች ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስገንዝበዋል። 

የደብረ ብርሃን 04 ጤና ጣቢያ ስራ አስኪያጅ አቶ መኮንን አይተንፍሱ በበኩላቸው፤  የጤና ተቋማትን ደረጃ የማሻሻል ስራ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል። 

መምሪያው በእለቱም በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ የስራ አፈፃፀም ላላቸው የጤና ተቋማትና ከመገናኛ ብዙሃን ደግሞ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ጨምሮ ለሌሎች አጋር አካላት የምስጋና የምስክር ወረቀት አበርክቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም