ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት የሚያስችል ታሪካዊ አጋጣሚ ነው 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2018 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምክክሩ የወደፊት የጋራ ኢትዮጵያን የምንገነባበት ታሪካዊ መድረክ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አሕመድ ሁሴን ገለፁ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አሕመድ ሁሴን በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ አሁን የተደረሰበት የምክክር ምዕራፍ በበርካታ ባለድርሻ አካላትና ሀገር ወዳድ ዜጎች ከፍተኛ ልፋት፣ ድካምና መስዋዕትነት የተገኘ ነው። 

በመሆኑም ሂደቱን በመምራት እዚህ እንዲደርስ ላደረገው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ ለኮሚሽነሮቹና ለመንግስት ምስጋና አቅርበዋል።

ዛሬ የተጀመረው ምክክር የወደፊት የጋራ ኢትዮጵያ የሚገነባበት ትልቅ መድረክ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ተመካካሪዎች በተመረጡት አጀንዳዎች ላይ የዜጎችን እውነተኛ ፍላጎትና ተስፋ መሰረት አድርገው በመምከር ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያመጡ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የሲቪል ማህበራት ለፖለቲካ ያልወገኑና ለትርፍ ያልተቋቋሙ በመሆናቸው በመሃል መንገድ በመቆም የመተማመን ድልድይ የመገንባት፣ የተገለሉ ድምጾችን የማሰማትና የሰላማዊ ምክክር ባህልን የማጠናከር ልዩ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። 

ይህ ታሪካዊ ሂደት ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እያንዳንዱ ዜጋና ባለድርሻ አካል በባለቤትነት ስሜት እንዲሳተፍ ሂደቱንም በጽኑ እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም