ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ የፖለቲካ ስልጣን በኃይል ሳይሆን በህዝብ ፍላጎት ብቻ የሚገኝበትን ስልጡን ስርዓት ለመገንባት መሰረተ የሚጣልበት ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የፖለቲካ ስልጣን በጠመንጃ ሳይሆን በሰለጠነ የፖለቲካ ባህልና በህዝብ ፍላጎት ብቻ የሚገኝበትን ስርዓት ለመገንባት መሰረት የሚጣልበት ነው ሲሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በይፋ ተጀምሯል።

በዚሁ መድረክ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ እንደተናገሩት፤ ጉባኤው ታሪካዊና ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ህዝቦች በጉጉት ሲጠብቁት የነበረውን ይህን ጉባኤ የዚህ ዘመን ትውልድ እውን እንዳደረገው ጠቅሰዋል።

ጉባኤው የፖለቲካ ስልጣን በጠመንጃ ሳይሆን በሰለጠነ የፖለቲካ ባህልና በህዝብ ፍላጎት የሚገኝበትን ስርዓት ለመገንባት መሰረት የሚጣልበት መድረክ ነው ሲሉም ጠቅሰዋል።

ሀገሪቱን ከግጭት አዙሪት በማውጣት፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት የሚያስችል ባህል ለመገንባት የሚደረግ ትልቅ ጉዞ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግባባትን መፍጠርና በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ሀገርን ከማጽናት አንጻር በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክር የፖለቲካ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍትሄ መፈለጊያ፣ የሰላም ግንባታ መሳሪያና የፖለቲካ ሽግግር ማሳለጫ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና አባል የፖለቲካ ድርጅቶች ዛሬ ላይ የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር የተሳካ እንዲሆንና የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ሙሉ ለሙሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም