ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በውጭ ፕሮፓጋንዳ ተጠምዳ ጥቅሟን አሳልፋ ትሰጣለች ብሎ መገመት ከንቱ ምኞት ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2018(ኢዜአ)፦ ለሺህ ዓመታት ጸንታና በቀላሉ በማይበጠስ ጠንካራ ትስስር ተሰናስላ የኖረችው ኢትዮጵያ በውጭ ፕሮፓጋንዳ ተጠምዳ ጥቅሟን አሳልፋ ትሰጣለች ብሎ መገመት ከንቱ ምኞት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በይፋ ተጀምሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ ታሪክ ጠገብና ጥንታዊ ሀገር መሆኗን አስታውሰው፣ በውስጥ የሚከሰቱ ችግሮች በሙሉ እኛው ጀምረን እኛው የምንጨርሳቸው ብቻ እንዳልሆኑ ገልጸዋል።

በሀገሪቱ ውስጥ ኮሽ ሲል የሚነቁና የዘመናት ያልተቋረጠ የጠላትነት ታሪክ ያላቸው ኃይሎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።


 

ኢትዮጵያ ስትገነባ የማይታዩ፣ ነገር ግን አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ጣልቃ የሚገቡ ጊዜ ጠባቂ ኃይሎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ በቅርቡ ቀይ ባሕርን ያጣንበት አጋጣሚ የዚህ እኩይ ታሪካዊ ክስተት የእኛን ስንፍና የመጠቀምና የጣልቃ ገብነት አንዱ መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለሺህ ዘመናት ያስተዳደረችውን፣ በባለቤትነት የያዘችውንና ለራሷም ሆነ ለአካባቢው መጠቀሚያ ያደረገችውን ቀይ ባሕር፣ ያልተመረጠ፣ ያልተወያየ መንግሥት በሸፍጥ ኢትዮጵያን የጂኦግራፊ እስረኛ እንድትሆን ማድረጉን አስታውሰዋል።

ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት የኢትዮጵያን ብሔራዊ መሻትና ጥቅም ማስቆም የሚችል ኃይል ስለነበረ፣ ስላለና ስለሚኖር ሳይሆን በውስጥ ስንፍናችን በተፈጠረ ድክመት ነው ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሲገነባ፣ ከተሞች ሲያሸበርቁና ሌሎች የልማት ሥራዎች ሲጀመሩ አብረው ያልነበሩ ኃይሎች፣ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ሲጨቃጨቁና የውስጥ ችግሮች ሲፈጠሩ ግን ገንዘብ፣ መሣሪያና የሚዲያ ፕሮፓጋንዳ ሲያቀብሉ እንደሚታዩም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሕዝብ በማንኛውም የውስጥ ጉዳይ ላይ ቢለያይና ቢከራከር እንኳን፣ ጉዳዮችን በውይይት መድረኮች መፍታት እንደሚቻል አስገንዝበዋል።

በውስጥ ጉዳይ ላይ መከራከርና መወያየት መብት መሆኑን ገልጸው፤ ለሌሎች ኃይሎች ጥቅም ሲባል የኢትዮጵያን ብሔራዊ ፍላጎት አሳልፎ የሚሰጥ "እንክርዳድ" መሆን እንደማይገባና ሁሉም ዜጋ በንቃት እንዲሠራ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ለሚያንዣብቡ አሞሮች ሲሉ ለገለጿቸው የውጭ ኃይሎች ጠንከር ያለ መልዕክትም አስተላልፈዋል።

ከብቱን መርጠን የምንገዛው፣ የቅርጫውንም ባለቤት የምንወስነው እኛ ነን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ካልተረፋትና በራሷ ፈቃድ ካልሰጠች በቀር፣ አሁን በሚነዛ የውጭ ፕሮፓጋንዳ ተዘናግታ ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፋ ትሰጣለች ብሎ መገመት ፈጽሞ ከንቱ ምኞት መሆኑን አስገንዝበዋል።


 

የውጭ ኃይሎች ለሺህ ዓመታት ጸንታ የኖረችውና በቀላሉ በማይበጠስ ጠንካራ ትስስር ተሰናስላ የኖረችውን ሀገር ታሪክ በትክክለኛው መንገድ በመረዳት፣ ወደ ቀልባቸው ተመልሰው ለጋራ ጥቅም በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ መከራዎችን አልፋ እንድትጸና ያደረጋት ያላት የችግር መፍቻ ሀብት መሆኑንና ኢትዮጵያውያን ከተደማመጡና ከተመካከሩ ሀገር ማጽናት እንደሚቻል ገልጸው፤ ምክክሩ ስኬታማ የሚሆነው የጋራ መፍትሔ ሲገኝ ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ አራት ሺህ ተመካካሪዎችን በመሰብሰብ ሁሉን አቀፍ ምክክር መጀመሯን ገልጸው፤ ተመካካሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በጉባኤው አዳራሽ ውስጥ ልባቸውንና አዕምሯቸውን ሰብስበው ሌላውን ወገን ማዳመጥ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።

ምክክሩ ከአዳራሹ ወጥቶ እንደ ፀሐይ ለመላው ኢትዮጵያ እንዲያበራና ለተተኪው ትውልድ የጸናች ሀገርን ለማስረከብ እንዲያስችል ሁሉም ዜጋ በጎ አሻራ እንዲያሳርፍ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም