ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያ በገዛ እጇ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ የሚያስችላትን “ብዕርና ብራና” ያገኘችበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያ በገዛ እጇ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ የሚያስችላትን “ብዕርና ብራና” ያገኘችበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ኢትዮጵያ በገዛ እጇ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ የሚያስችላትን “ብዕርና ብራና” ያገኘችበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ግዙፍና ታላቅ ዓላማ ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ በዚህ ታሪካዊ ሀገራዊ ምክክር የማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለመታደም በመታደሌ ታላቅ ኩራት ይሰማኛል ብለዋል።
በሚቀጥሉት ሳምንታት አራት ሺህ ተሳታፊዎችን በአንድ ጣሪያ ስር የሚያሰባስበው ይህ ታላቅ ጉባኤ፣ ኢትዮጵያ በገዛ እጇ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ የሚያስችላትን “ብዕርና ብራና” ያገኘችበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞ በኃይለ ቃል ጀምሮ በኃይለ እርምጃ የሚደመደምበትን አዙሪት ሰብረን በንግግርና በውይይት የምንተካበት ወቅት ላይ እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።
ለዚህ ታላቅ ጉዞ መሳካት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ያለኝን ታላቅ ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ ብለዋል።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በማሳተፍ ከሥር ወደ ላይ በዘለቀው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት ላይ የተመሰረተው ይህ ጉባኤ፣ በቀላሉ የማይደገም እና በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ግዙፍና ታላቅ ዓላማ ያለው መሆኑን አስገዝንዘዋል።
በዚህም ፈተናዎቻችንን ወደ መልካም አጋጣሚዎች በመቀየር ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ባህልን እናጸናለን ሲሉ ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለት ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ መልካም ዘሮችን እንዘራለን፤ ከሚያፈራውም ፍሬ ልጆቻችን መጠቀም እንዲችሉ እናደርጋለን ነው ያሉት።
በዚህ ምክክር ላይ ስንሳተፍ ከየሰፈራችን ወጥተን ለኢትዮጵያ ስንመክር፣ ለልጆቻችን ስንልና እነርሱን እያሰብን ስንወያይ ውጤቱ እጅግ ፍሬያማ እንደሚሆንም ነው የገለጹት።
አብረን ተስፋን፣ ይቅርታን እና በጋራ መኖርን እንትከል፤ በሀገር ውስጥ በሚደረግ ውይይትና ይቅርታ ችግሮቻችንን በመፍታት ሀገራችንን ከውጭ ጣልቃ ገብነት እንጠብቅ በማለት አሳስበዋል።
ተሳታፊዎች በሙሉ ለኢትዮጵያ መልካም፣ ለአፍሪካ አስተማሪ፣ ለመላው ኢትዮጵያውያን ደግሞ እውነተኛ እረፍትን የሚያመጣ ታሪካዊ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።