ኢትዮጵያ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ዛሬም እንደ ትናንቱ ለአፍሪካ ምሳሌ ሆና ትቀጥላለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ዛሬም እንደ ትናንቱ ለአፍሪካ ምሳሌ ሆና ትቀጥላለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ፈተናዎችን ወደ መልካም ዕድል በመቀየር ዛሬም እንደ ትናንቱ ለአፍሪካ ምሳሌ ሆና እንደምትቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በመካሄድ ላይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ከተጋረጡባት ማዕበልና መከራዎች የምትሸሽ ሳትሆን፣ ፈተና እና መከራዎችን በጽናት አልፋ ወደ ዕድል የመቀየር የታሪክና ልምድ ያላት ሀገር መሆኗን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ትበለፅጋለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ፈተናዎችን አልፋ ዛሬም እንደ ትናንቱ ለአፍሪካ ምሳሌነቷን አስከብራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።
የጀመርናቸውን መልካም ዘሮች እንዘራለን፣ እንንከባከባለን፣ ዛፍም እናደርጋቸዋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የእነዚህን መልካም ሥራዎችና የልማት ፍሬዎች ዛሬ ላይ ያሉት ሳይሆኑ፣ መጪው አዲስ ትውልድ እንዲጠቀምባቸው ታስቦ እየተሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ የምክክር ጉባኤ በተወከሉ ተመካካሪዎች ለትውልድ የሚበጅና ዘላቂነት ያለው ሐሳብ እንድታመነጭ እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።