ቀጥታ፡

ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ኢትዮጵያ ለመድረስ ያለመችበትን ግብ የምታሳካበት ታላቅ ዕድል ነው - ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ኢትዮጵያ ያስቀመጠቻቸውን ግቦች ማሳካት የሚያስችል ታላቅ ዕድል መሆኑን የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ቺፍ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መክፈቻ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬሽን ማዕከል እየተካሄደ ይገኛል።


 

የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ቺፍ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ፤ ዛሬ የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው እና ለአፍሪካ ታሪካዊ የሚባል ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ የውስጥ ችግሮቻቸውን በውይይት እና በንግግር ለመፍታት የመረጡት መንገድ እንደሚያመሳስላቸውም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዚህ ታሪካዊ እጥፋት ላይ ሆኖ ያከናወናቸውን ተግባራትና ዝግጅቶች አድንቀዋል።

ኦባሳንጆ የምክክር ኮሚሽኑን የመጎብኘት እድል እንዳገኙና በተመለከቷቸው ነገሮች መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ህዝቧ፣ የተፈጥሮ ሀብቷ እና የኢኮኖሚ ዘርፉን ጨምሮ በርካታ እድሎች እና አማራጮች ያላት ሀገር መሆኗንም አመልክተዋል።

ስንዴ ከውጭ ማስገባት አቁማ ምርት በራሷ አቅም ከማምረት ባለፈ ወደ ውጭ እስከ መላክ መድረሷን ጠቅሰው ይህም የአፍሪካ የምግብ ቅርጫት እንድትሆን የሚያስችላት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለማደግ እና ለመለወጥ በርካታ አቅሞች አሏትም ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

ኢትዮጵያ ትልሞቿ እና ውጥኖቿን እውን ለማድረግ የተሳካ ሀገራዊ የምክክር ሂደት ማከናወን እንደሚጠበቅባት አመልክተዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ የወደፊት ግቦች መሳካት ጉልህ አበርክቶ እንዳለው ጠቅሰው ይህም በአፍሪካ እና በዓለም ደረጃ ያላትን የመሪነት ሚና እንደሚያሳድገው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም