ቀጥታ፡

ልዩነቶችን በምክክር መፍታት ለኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ይከፍታል - ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2018 (ኢዜአ)፦ልዩነቶችን በምክክር መፍታት ለኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንደሚከፍት የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በመካሄድ ላይ ነው። 


 

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ይህ ታሪካዊ የምክክር ጉባኤ በኢትዮጵያ ረዥምና ኩሩ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ወሳኝ ክስተትና ቀኑም ለሀገሪቷ ታሪካዊ ነው።

በዓለም ታሪክ ውስጥ በግጭት የተሠራ፣ የተገነባ ወይም ያተረፈ ሀገር አለመኖሩን በአጽንኦት ገልጸዋል። 

ዛሬ የተሻለ ደረጃ ላይ የደረሱ ሀገራት ስኬታማ ሊሆኑ የቻሉት ሀገራዊ ጥቅማቸውን በማስቀደም፣ በመደማመጥና በመነጋገር መሆኑን ጠቅሰው፤ ልዩነቶች መፈታት የሚችሉት በሰላማዊ መንገድና በውይይት ብቻ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ማንነቷን የምትፈልግ አዲስ ሀገር ሳትሆን በምድር ላይ ካሉ ጥንታዊና ጠንካራ ሥልጣኔዎች መካከል አንዷ መሆኗን የገለጹት ዋና ጸሐፊው፤ በታሪክ፣ በባህልና በእምነት ውስጥ ጥልቅና ውብ የሆኑ የእርቅና የማስታረቅ ሥርዓቶች እንዳሉ አስታውሰዋል። 

ጥንታዊ የሀገር ባህል ችግር መፍቻ መፍትሔዎች ኢትዮጵያ የራሷን ቁስል የምታክምባቸው ቁልፍ መሣሪያዎች ናቸው ብለዋል።

ለችግሮች መፍትሔ ወደ ውጭ ማማተር አያስፈልግም ያሉት ዋና ጸሐፊው፤ ትኩረት ሊደረግ የሚገባው በሀገር ውስጥ ባሉ በርካታ አዎንታዊና አርአያነት ያላቸው ምሳሌዎች ላይ ነው ብለዋል። 

ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን በምክክርና በጋራ መከባበር መፍታት እንደሚችሉ በተግባር የምናስመሰክርበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ታሪክ ወደፊት የሚሠራው በመነጋገር እንደሆነ ገልጸው፤ ተመካካሪዎች ማንኛውንም ጉዳይ በምክክር እንዲፈቱ አደራ ብለዋል። 

ኢጋድም በዚህ ታሪካዊ ጉዞ ውስጥ ከኢትዮጵያ ጎን በጽናት እንደሚቆም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም