ቀጥታ፡

በኃይለ ቃል ተጀምሮ በኃይል እርምጃ የሚደመደመውን የፖለቲካ ስብራት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማቆም ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2018(ኢዜአ)፦ ፖለቲካችን በኃይለ ቃል ይጀምራል፣ በኃይል እርምጃ ይደመደማል ይህንን ስብራት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማቆም ያስፈልጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በመካሄድ ላይ ነው።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት መከራና ችግር በውስጣቸው ዕድልና መፍትሔ የያዙ ናቸው ብለዋል።

ያለፉትን ፈተናዎች በምክክር በመሻገር ለልጆቻችን የተሻለ ሰላም፣ ብልፅግና እና የኑሮ ዘይቤ ለመፍጠር መጣር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

መንግሥት ባለፉት ዓመታት የተገኙ ዕድሎችን በአግባቡ በመጠቀም በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ሪፎርሞችን ማካሄዱን ጠቅሰው፤ አዲስ አበባም በኮሪደር ልማት ከነበረችበት ቆሻሻ ተላቃ አዲስና ውብ መልክ መያዟን ተናግረዋል።

አራት ዓመት የፈጀው አድካሚ ሂደትና ሁሉን አቀፍ የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ያስፈለገው፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የሚታየውን ስብራት ለመጠገን መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እጅግ ታሪክ ጠገብና የሰው ልጅ መገኛ ብትሆንም፣ በፖለቲካ ጉዞዋ ሁልጊዜ በኃይለ ቃል ጀምሮ በኃይል እርምጃ የመደምደም ልምድ መኖሩን አስታውቀዋል።

ይህንን የኃይል እርምጃ የታሪካችን አካል የማድረግ የተሳሳተ አካሄድ ለአንዴና ለዘለቄታው ማቆም እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በታሪካችን ውስጥ ስንጨቃጨቅ ጊዜ ጠብቀው እየገቡ መሻቶቻችንን እንዳናሳካ የሚያደርጉ የውጭ ኃይሎች መኖራቸውን በማውሳት፣ በቅርቡ ቀይ ባሕርን ያጣንበት አጋጣሚ የዚህ እኩይ ታሪካዊ ክስተት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲህ ያሉ መጥፎ አጋጣሚዎች እንዳይደገሙና የተፈጠሩ ስብራቶችን ለመጠገን ዛሬ የምናገኛትን እያንዳንዷን ደቂቃ እንደ ታላቅ ዕድል በመቁጠር፣ የኢትዮጵያን ብልፅግና በአስተማማኝ መሠረት ላይ ለመገንባት ሳንታክት መስራት ይገባልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም