የተገኘውን ታላቅ የምክክር ዕድል በኃላፊነት ስሜት ልንጠቀምበት ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የተገኘውን ታላቅ የምክክር ዕድል በኃላፊነት ስሜት ልንጠቀምበት ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2018 (ኢዜአ)፦ የተገኘውን ታላቅ የምክክር ዕድል በኃላፊነት ስሜትና በአክብሮት ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በመርሐግብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ ይህ ጉባዔ በቀላሉ የማይደገም፤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ የገዘፈ ዓላማ ያለውና ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን ሁሉን አቀፍ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አንዳንድ አጋጣሚዎች ያሻችሁን እንድትጽፉ ብዕርና ብራና ያቀብሏችኋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዛሬው መድረክም የታሪክ አጋጣሚውን ማዝለቅ ለፈለጉ ሰዎች በዚያ ብዕርና ብራና ላይ ሀገርን የሚገነባ ለዘመናት የሚታወስ ታሪክ ለመጻፍ እድል የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በተቃራኒው ይህንን እድል የማይጠቀሙ እና ሀገርን ከሚገነባ ይልቅ የሚያፈርስ ታሪክ ጽፈው የሚያልፉ መኖራቸውንም አንስተዋል፡፡
በመሆኑም ይህ ታሪክ ዛሬ እንደይደገም ምክክሩ በኃላፊነት ስሜትና በታላቅ አክብሮት ሊከናወን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
እኛ እና ከእኛ በፊት የነበሩ ሰዎች ያጧቸውን ጉዳዮች ዳግም ልጆቻችን እንዳያጡ በታላቅ ኃላፊነት ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ችግር ወደ ዕድል መቀየር ከተቻለ የተሻለ ትውልድ መፍጠር እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
ይህንን ለማምጣት የምክክሩን መልካም አጋጣሚ ወደ ዕድል መቀየር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
መሰል ዕድል ሲገኝም በኃላፊነት ስሜት በቅጡ የምንጠቀምበት ከሆነ እድል ደጋግሞ ወደ እኛ ይመጣልም ነው ያሉት፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተገኘውን እድል ሁሉ በመጠቀም በኢትዮጵያ የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ እና የወታደራዊ ሪፎርም በማካሄድ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን በማስታወስ ለዚህም የአዲስ አበባ ከተማን ልማት ለአብነት አንስተዋል፡፡
ዛሬም በምናገኘው እያንዳንዱን እድል በመጠቀም ለኢትዮጵያ ብልጽግና መሰረት ለመጣል እንተጋለን ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡