የምክክር ጉባኤው ሀገርን የሚታደግና የሚገነባ ታሪክ ለመጻፍ ታላቅ እድል የሚሰጥ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ጉባኤው ሀገርን የሚታደግና የሚገነባ ታሪክ ለመጻፍ ታላቅ እድል የሚሰጥ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2018(ኢዜአ)፦ የምክክር ጉባኤው ሀገርን የሚታደግ፣ የሚጠቅም፣ የሚገነባና ለዘመናት የሚታወስ ታሪክ ለመጻፍ እድል የሚሰጥ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በመካሄድ ላይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ በስፋቱ፣ በአካሄዱ እና በሚያስገኘው ውጤት ታላቅ ዓላማና ተግባር ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ መድረክ ኢትዮጵያን ለሚወከሉ የተዘጋጀ ሁሉን አቀፍ መድረክ መሆኑን በመጥቀስ፣ አጋጣሚዎች ከታሪክ ብዕርና ብራና ፊት እንደሚያቆሙን ጠቅሰዋል፡፡
ይህ የዛሬው መድረክ ሀገርን የሚታደግና የሚገነባ ታሪክ ለመጻፍ ታላቅ እድል የሚሰጥ እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ይህንን እድል የማይጠቀሙና ደጋግሞ እንደማይገኝ የማይገነዘቡ አካላት ታሪክ ሲገኝ ሀገርን ከሚገነባ ይልቅ የሚያፈርስ ታሪክ ጽፈው እንደሚያልፉ አስታውሰዋል።
ስለሆነም ይህ ታሪካዊ የምክክር ዕድል በቀላሉ የማይገኝና ሊደገም የማይችል በመሆኑ፣ እኛ እና ከዚህ በፊት የነበሩ ሰዎች ያጧቸውን እድሎች ልጆቻችን እንዳያጡ በታላቅ አክብሮት ልንከውነው ይገባል ብለዋል።
የምክክሩ ተሳታፊዎች በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜትና በትህትና ለምክክር ጉባኤው መሳካት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
#በምክክር_የምትጸና_ሀገር_ኢትዮጵያ