ቀጥታ፡

ጉባኤው ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ እና አስተማማኝ ሀገር መገንባት የሚያስችል ትልቅ ዕድል ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክከር ጉባኤ ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ እና አስተማማኝ ሀገር መገንባት የሚያስችል ትልቅ ዕድል መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ፡፡ 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተጀምሯል።

ይህ ታሪካዊ መድረክ በኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት እና ለትውልድ የሚሻገር እንደሆነም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በጉባኤው ላይ ባደረጉት መክፈቻ ንግግር፤ ጉባኤው በሀገራችን የፖለቲካ እና ማህበራዊ ጉዞ አቅጣጫን የሚያቀና መሆኑን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክና የብዝሃነት ውበት ባለቤት መሆኗን ጠቁመው፤ በዘላቂነት ለማስቀጠል የሚረዱ በርካታ የሀሳብ ልዩነቶች እና አለመግባባቶች ፈተና ሆነው ቆይተዋል ብለዋል።

በተለይም ለዘመናት የተከማቹ የፖለቲካ እና የስርዓት ጥያቄዎች ዛሬም ድረስ የዜጎችን ሰላም እና የሀገር አንድነትን እየፈተኑ ይገኛሉም ብለዋል።

የሀሳብ ልዩነት በራሱ ችግር እንዳልሆነና የተለያዩ አመለካከቶች የዴሞክራሲያዊ ሕይወታችን አካል መሆናቸውን የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ችግሩ የሚጀምረው እነዚህን ልዩነቶች በምክክር ፈንታ በኃይል፣ በግጭት ወይም በመገዳደል ለመፍታት ሲሞከር እንደሆነ አስታውቀዋል።

ስር የሰደዱ ችግሮችን በኃይል፣ በጊዜያዊ ማስታገሻዎች ወይም በአግላይ ሂደቶች በዘላቂነት መፍታት እንደማይቻል ታሪክ ያስተማረን መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ብቸኛው እና ዘላቂ መፍትሄ ታማኝ፣ አካታች፣ ግልጽ እና ሳይንሳዊ የሆነ ሀገራዊ ምክክር ማካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።

ጉባኤው ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ ይዞ በጋራ መኖር የምንችልበትን ስርዓት የምንዘረጋበት መድረክ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በተጨማሪም እርስ በእርስ መደማመጥን፣ የሌላውን ህመም መረዳትን፣ የቆዩ የታሪክ ጠባሳዎችን መሻርን እና በጋራ የወደፊት የሀገሪቱ እጣ ፈንታ ላይ መግባባትን የሚፈጥር ሀገራዊ ፈውስ የሚከናወንበት እንደሆነ አስረድተዋል።

ይህ ጉባኤ ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ እና አስተማማኝ ሀገር መገንባት የሚያስችል ትልቅ ዕድል እንደሚሰጥም ነው ያስገነዘቡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም