ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለሀገር ዕድገትና ለሕዝቦች አንድነት መጠናከር መሰረት የሚጣልበት እንዲሆን የሃይማኖት አባቶች መልካም ምኞታቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2018(ኢዜአ)፦ ዛሬ የተጀመረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለሀገር ዕድገትና ለሕዝቦች አንድነት መጠናከር መሰረት የሚጣልበት እንዲሆን እንመኛለን ሲሉ የሃይማኖት አባቶች ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ መክፈቻ መርሃ ግብር በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በመካሄድ ላይ ነው።

ታሪካዊ የምክክር ጉባኤውን የሃይማኖት አባቶች በጸሎትና በቡራኬ በይፋ አስጀምረውታል።

በመክፈቻ መርሃ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የፓትርያርኩ ተወካይ ብጹዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ ጉባኤው ለሀገር ዕድገትና ለሕዝብ አንድነት የሚበጅ መልካም ፍሬ እንዲያፈራ ተመኝተዋል።

ፈጣሪ መሪዎቻችንን በሰላምና በጤና ይጠብቅልን በማለትም መሪዎች ሕዝባቸውን በፍቅርና በእውነት ማገልገል እንዲችሉ ጥበብን እንዲሰጣቸው መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው፣ ዘመኑ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ይህ ታሪካዊ መድረክ ውጤታማ እንዲሆንና ሁሉም በአንድ ልብ መምከር እንዲችል የፈጣሪን እገዛ የጠየቁት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም፣ አሁን ላይ ፊታችንን ሰላምን ወደሚያጸኑና ወደ ልማት ጉዳዮች ማዞር እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌልም ምክክሩ ሰላምና አንድነት የሚጸናበት እንዲሆን ተመኝተዋል።

በምክክር አማካኝነት ችግሮቻችንን በሙሉ በመፍታት በአርአያነት የምትጠቀስ ሀገር መገንባት እንድንችል ፈጣሪ ይርዳን ብለዋል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ፕሬዝዳንት ቄስ ደረጀ ጀንበሩ፣ ይህ ጉባኤ ለሀገር ከፍታ የሚያመጣ ይሆን ዘንድ እያንዳንዳችን በማስተዋልና በጥበብ ልንሳተፍ ይገባል ብለዋል።

የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን ፕሬዝዳንት ፓስተር ታደሰ አዱኛም ፈጣሪ አንድነታችንን እንዲገነባ መልካም ምኞታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ መድረኩ የጋራ መግባባትንና መቀራረብን የሚያጠናክር እንደሚሆንም ተመኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም