የጅማ ዞን አርሶ አደሮች ቡናን በጥራት ለገበያ በማቅረባቸው ተጠቃሚ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
የጅማ ዞን አርሶ አደሮች ቡናን በጥራት ለገበያ በማቅረባቸው ተጠቃሚ ሆነዋል
ጅማ፤ ሐምሌ 8/2018 (ኢዜአ)፦ ቡናን በጥራት ለገበያ በማቅረባቸው ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን የጅማ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።
አርሶ አደሮቹ ከልማዳዊ አሰራር በመላቀቅ ቡናን በባለሙያ ታግዘው በማልማትና በማዘጋጀት ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የጅማ ዞን ጮራ ቦቶር ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሁሴን ቶላ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በግብርና ምርምር ማዕከልና በግብርና ጽሕፈት ቤት ባለሙያዎች ታግዘው የቡና ጥራትን ለማሻሻል ሲሰሩ ቆይተዋል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርት የሚሰጥና በሽታን የሚቋቋም የቡና ዝርያን ማልማታቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ቡናን ከምርት ጀምሮ ለገበያ እስከሚቀርብበት ጊዜ ድረስ ለጥራት ትኩረት መስጠታቸውን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት እስካሁን 5ሺህ ኪሎግራም ጥራቱን የጠበቀ ደረቅ ቡና አዘጋጅተው ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ የገበያ ትስስር ችግር እንደሌለና በመንግስት በኩል ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት መሰጠቱ ተነሳሽነታቸው እያደገ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከአራት ዓመታት በፊት በግብርና ጽሕፈት ቤት ድጋፍ የተሻሻለ የቡና ዝርያ ቀርቦላቸው ማልማታቸውን የተናገሩት ደግሞ አርሶ አደር ታጁ ያደታ ናቸው።
ቡናን ከአመራረት ጀምሮ በዝግጅትና ለገበያ እስከማቅረብ ሂደት ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን የባለሙያ ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ዘንድሮ የቡና ምርታቸውን በጥራት በመሰብሰብና በማዘጋጀት ለገበያ ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል።
በዘርፉም ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የስራ ዕድል መፍጠራቸውን አስታውቀዋል።
የጅማ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሚፍታህ ጋሊ፣ ዞኑ በቡና ምርት የሚታወቅ እንደመሆኑ ለምርቱ ጥራት ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል ።
በተለይም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የገበያ ትስስርን በማስፋት፣ ለአምራቹ በቂ ግንዛቤና ስልጠና በመስጠት እንዲሁም ክትትል በማድረግ ትልቅ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት አመት ጥራቱን ጠብቆ የተዘጋጀ 102 ሺህ ቶን ቡና ለገበያ መቅረቡን ጠቁመው ለገበያ ከቀረበው ቡና ውስጥ 41 ሺህ ቶኑ የታጠበና ቀሪው ደረቅ መሆኑን ተናግረዋል።
የቡና ልማትን ለማስፋፋትና ጥራቱን የበለጠ ለማሳደግ የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን በማዘጋጀት ለአርሶ አደሩ የማድረስ ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።
ዘንድሮም 700 ሚሊዮን የቡና ችግኞችን በማሰራጨት ተከላው እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።