በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስፖርት መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ብቁ ዜጋ የማፍራት ሥራ ተጠናክሯል - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስፖርት መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ብቁ ዜጋ የማፍራት ሥራ ተጠናክሯል
ወልቂጤ፤ ሐምሌ 8/2018 (ኢዜአ)፦ በክልሉ የስፖርት መሰረተ ልማትን በማስፋፋት በአካልና በአዕምሮ የዳበረ ዜጋን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።
በወልቂጤ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተገኙበት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መርሃ ግብር ተካሄዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ሌሊሾ እንደገለጹት፤ በክልሉ የስፖርት ልማትን በማስፋፋት በአካልና በአዕምሮ የዳበረ ጤናማና ብቁ ዜጋ ለማፍራት እየተሰራ ነው።
ለዚህም በየአካባቢው የስፖርት ማዘወተሪያዎችን ከማስፋፋት ባለፈ ስፖርትን ባህሉ ያደረገ ማህበረሰብ ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተው፣ የዛሬው ስፖርታዊ እንቅስቃሴም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።
በተለይ ወጣቶች ስፖርትን በማዘወተር ያላቸውን ተሰጥኦ እንዲያጎለብቱ መሰራቱን ገልጸዋል፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴው የእርስ በርስ ትስስርንም ያጠናክራል ብለዋል።
የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር በበኩላቸው፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከጤና ጥቅሙ ባለፈ የዜጎችን የአብሮነት እሴት የሚያጎለብትና በራሱ የሚተማመን ትውልድ ለመቅረጽ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም ከተማዋ በብስክሌት፣ በቅርጫት ኳስ፣ በእግር ኳስ ጠንካራ ስፖርተኞች ለማፍራት የሚያስችል የስፖርት መሰረተ ልማቶችን እየገነባች መሆኑን አክለዋል።
ይህም ለከተማዋ ኢኮኖሚና የስፖርት ቱሪዝም መነቃቃት ጉልህ ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ከተሳታፊዎች መካከል ኢንስፔክተር አብድልሰመድ መሃመድ፤ በከተማዋ የስፖርት ልማቱን የሚያቀላጥፉ መሰረተ ልማቶች መከናወናቸው የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መርሀግብሩ በስፖርት ጤናማና ብቁ ዜጋ ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት አጋዥ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ ካሚል ጀማል ናቸው።
መርሀግብሩ የእርስ በርስ ግንኙነትን በማጠናከር የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን በጋራ ለማከናወን ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸውም ጠቅሰዋል።