በዞኖቹ የተተገበሩ አዳዲስ የግብርና ልማት ኢኒሼቲቮች የአርሶ አደሮችን ሕይወት በተጨባጭ እየቀየሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኖቹ የተተገበሩ አዳዲስ የግብርና ልማት ኢኒሼቲቮች የአርሶ አደሮችን ሕይወት በተጨባጭ እየቀየሩ ነው
አዳማ ፤ ሐምሌ 8/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል በኢሉ አባቦር እና ባሌ ዞኖች የተተገበሩ አዳዲስ የግብርና ልማት ኢኒሼቲቮች የወጣቶችንና የአርሶ አደሮችን ሕይወት በተጨባጭ እየቀየሩ መሆኑን የዞኖቹ አስተዳዳሪዎች ገለጹ።
በአዳማ አባ ገዳ አዳራሽ እየተካሄደ በሚገኘው የክልል መንግሥት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ላይ የተሳተፉ የዞን አስተዳዳሪዎች እንደተናገሩት ኢኒሼቲቮቹ በሁሉም መልኩ ስኬታማ እየሆኑ ነው።
የኢሉ አባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ፤ ዞኑ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ወደ ዕድል በመቀየር በሁሉም ረገድ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ለውጥ እያመጡ ነው ብለዋል።
ዞኑ በተፈጥሮ ደን የበለጸገ መሆኑንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ በተሰጠው ትኩረት በተከናወነው ሥራ የደን ሽፋኑ መጨመሩን ገልጸዋል።
ይህንን ያለውን አቅም ወደ ዕድል በመቀየር ረገድ በተከናወነው ሥራ የማር ልማት ኢኒሼቲቭ በሰፊው የተሰራበት መሆኑን ጠቅሰው ይህም በተለይ ወጣቶችን እና አርሶ አደሮችን የበለጠ ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል።
በዚህም በየዓመቱ ዘመናዊ የንብ ማነቢያ ቀፎዎችን በማሰራጨት በዞኑ የማር ልማት በከፍተኛ ደረጃ እንዲስፋፋ መደረጉን አቶ እንዳልካቸው ገልጸዋል።
በማር ልማት ሥራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶችና አርሶ አደሮችም የማር ምርታቸውን እስከ ውጭ አገር ገበያ ድረስ በማቅረብ ሕይወታቸውን እየቀየሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዞኑ የሻይ ቅጠል ልማት ኢኒሼቲቭ ባለፉት ጥቂት ዓመታት አመቺ ሁኔታ ባላቸው ወረዳዎች ውስጥ እንዲስፋፋ በመደረጉ ኢኒሼቲቩ ለብዙዎች የሀብት ምንጭ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።
በባሌ ዞንም የግብርና ሥራን በሜካናይዜሽን በመደገፍ ምርታማነትን ለመጨመር የተከናወኑ አዳዲስ ኢኒሼቲቮች ውጤት ማምጣታቸውን የዞኑ አስተዳዳሪ ገልጸዋል።
በዚህም በዞኑ የግብርና ሥራን በሜካናይዜሽን በመደገፍ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እየተከናወነ ባለው ሥራ ተጨባጭ ውጤት እየተገኘ መሆኑን የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አሊይ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በዞኑ ከ72 በመቶ በላይ የሚሆነው የግብርና ሥራ በሜካናይዜሽን እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው በዓመት ከ800 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ተግባር ቀጥሏል ብለዋል።
በዞኑ በዓመት በክረምት፣ በበልግ ዝናብ እና በበጋ መስኖ ምርት እየተመረተ ሲሆን ይህም የአርሶ አደሩን የኑሮ ዘይቤ ከመቀየር ባለፈ ተጠቃሚነትን እያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በክልሉ ከተሞች የተተገበረውን የግብርና ኢኒሼቲቭ በመጠቀም የነዋሪውን ሕይወት ማሻሻል መቻሉን የተናገሩት ደግሞ የሞጆ ከተማ ከንቲባ አቶ ጋዛሊ ሀሹ ናቸው።
የከተማ ግብርና ኢኒሼቲቭ በተቀናጀ መንገድ ሥራ ላይ እየዋለ መሆኑን የገለጹት አቶ ጋዛሊ፤ የከተማዋ ነዋሪዎች የራሳቸውን ፍላጎት ከመሙላት አልፈው ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብ ሕይወታቸውንና ኑሯቸውን እየቀየሩ መሆኑን አስረድተዋል።
የከተማ ግብርና በግለሰቦችና በተለያዩ ተቋማት ባዶ ቦታዎች ላይ በዘመናዊ መንገድ የተለያዩ ምርቶች እንዲመረቱ በማድረግ የምርት አቅርቦት እጥረትን እየቀረፈ መሆኑንም አንስተዋል።
ይህ የከተማ ግብርና ኢኒሼቲቭ ያሉትን ዕድሎች ሁሉ በመጠቀም እንዲለማ መደረጉ የከተማዋን ነዋሪ የሥራ ባህል ከመሠረቱ እየቀየረው መሆኑንና በርካታ ሥራ ፈላጊ ወጣቶችም ተደራጅተው በከተማ ግብርና ላይ በመሰማራት ኑሯቸውን ከመሠረቱ እየቀየሩ መሆኑን ገልጸዋል።