በዞኑ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍኑ ችግኞት ይተከላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍኑ ችግኞት ይተከላሉ
ደሴ ፤ ሐምሌ 8/2018 (ኢዜአ)፦በሰሜን ወሎ ዞን በክረምቱ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍኑ ችግኞች እንደሚተከሉ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡
የሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተገኝ አባተ ለኢዜአ እንደገለጹት፣የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዞኑ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል።
መርሃ ግብሩ የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ፣ የአፈር ለምነት እንዲመለስ ፣በለሙ ተፋሰሶች ለወጣቱ የሥራ እድል እንዲፈጠር እና ምርታማነት እንዲያድግ ማድረጉን ነው የገለጹት።
በዘንድሮው ክረምትም ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ 169 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ከሚተከሉት ችግኝ ውስጥ ሁለት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን የሚሆነው የፍራፍሬ መሆኑን ጠቁመው ይህም የአርሶ አደሩንና የወጣቱን ዘላቂ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
ለዚህም የጉድጓድ ቁፋሮና ሌሎች ተያያዥ የቅደመ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ ለተከላ ዝግጁ የማድረግ ስራ መሰራቱን አስረድተዋል።
የሚተከለውን ችግኝ ከግጦሽና ከሰው ንክኪ በመጠበቅ የጽድቀት ምጣኔው ለማሳደግም ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ህብረተሰቡም ባለፉት ዓመታት ካለማቸው ተፋሰሶች እያገኘ ያለውን ጥቅም ለማስፋትም በያዝነው ክረምት በችግኝ ተከላው በንቃት ለመሳተፍ እንደተነሳሳም ተናግረዋል።
በዞኑ ራያ ቆቦ ወረዳ 08 የአራዱም ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰይድ ይመር፤ የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞችን በማፍላት በማሳቸው ላይ ተክለው ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዘንድሮም ከአንድ ሺህ በላይ የማንጎ፣ አቮካዶና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞችን ማዘጋጀታቸውን ጠቁመው ከተከላ የሚተርፈውን ሽጠው ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሰሜን ወሎ ዞን ባለፈው ክረምት ከተተከለው ችግኝ ውስጥ 78 በመቶ መጽደቁን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።