ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ማን ያልፋል? እንግሊዝ ወይስ አርጀንቲና? ተጠባቂው ፍልሚያ! - ኢዜአ አማርኛ
ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ማን ያልፋል? እንግሊዝ ወይስ አርጀንቲና? ተጠባቂው ፍልሚያ!
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 8/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ሁለተኛ የግማሽ ፍጻሜ መርሐ ግብር እንግሊዝ ከአርጀንቲና ዛሬ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ጨዋታው ምሽት አራት ሰዓት ላይ በአትላንታ ስታዲየም ይካሄዳል።
እንግሊዝ በሩብ ፍጻሜው ኖርዌይን 2 ለ 1 በማሸነፍ የመጨረሻ አራት ውስጥ ገብታለች። ሶስቱ አናብስቶች ለግማሽ ፍጻሜ ሲያልፉ የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ ነው።
ተጋጣሚዋ አርጀንቲና ስዊዘርላንድን 3 ለ 1 በመርታት ለግማሽ ፍጻሜ አልፋለች።
የወቅቱ የዓለም ሻምፒዮን አርጀንቲና አራት ውስጥ ስትገባ ለሰባተኛ ጊዜ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የደቡብ አሜሪካዋ ሀገር ከዚህ ቀደም ያደረጋቻቸውን ስድስት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች በሙሉ በማሸነፍ ስኬታማ ክብረ ወሰን አላት።
እንግሊዝ በበኩሏ ከሶስት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች መካከል ያሸነፈችው አንዱን ብቻ ነው።
ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ከዚህ ቀደም አምስት ጊዜ ተገናኝተዋል።
እ.አ.አ በ1962 በቺሊ በተካሄደው ሰባተኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ አራት ተገናኝተው እንግሊዝ አርጀንቲናን 3 ለ 1 አሸንፋለች።
እንግሊዝ እ.አ.አ በ1966 ባዘጋጀችው ስምንተኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ ላይ ተገናኝተው አዘጋጇ ሀገር 1 ለ 0 ያሸነፈች ሲሆን እስከ መጨረሻው በመጓዝ ምዕራብ ጀርመን (በወቅቱ በነበረው ስያሜዋ) በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች።
በሀገራቱ የዓለም ዋንጫ ግንኙነት ውስጥ ሁሌም የሚታወሰው ጨዋታ እ.አ.አ በሜክሲኮ አዘጋጅነት በተካሄደው 13ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በሩብ ፍጻሜው የተገናኙበት መርሐ ግብር ነው።
አርጀንቲና እንግሊዝን 2 ለ 1 በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜ አልፋለች። ዲያጎ ማራዶና ሁለቱንም ግቦች ከመረብ ላይ አሳርፏል።
በወቅቱ ማራዶና በእጁ ያስቆጠራት አወዛጋቢ ጎል “ የፈጣሪ እጅ” (Hand of God) እየተባለች ትጠራለች።
አርጀንቲና ፍጻሜ በመድረስ ምዕራብ ጀርመንን (በወቅቱ የነበረው አጠራሯ) በማሸነፍ ዋንጫውን ለሁለተኛ ጊዜ አንስታለች።
ፈረንሳይ እ.አ.አ በ1998 ባዘጋጀችው 16ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በሩብ ፍጻሜው መርሐ ግብር 16 ውስጥ ተገናኝተው በጨዋታ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቆ አርጀንቲና በመለያ ምት 4 ለ 3 በማሸነፍ ለሩብ ፍጻሜው አልፋለች።
ቡድኖቹ ለመጨረሻ ጊዜ በውድድሩ ላይ የተገናኙት ኮሪያ ሪፐብሊክ እና ጃፓን እ.አ.አ በ2002 ባዘጋጁት 17ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ላይ ነበር።
በምድብ ስድስት ባደረጉት ጨዋታ እንግሊዝ በዴቪድ ቤካም የፍጹም ቅጣት ምት ጎል 1 ለ 0 አሸንፋለች።
ሁለቱ ሀገራት ከ24 ዓመታት በኋላ በመድረኩ ለፍጻሜ ለማለፍ የሚያደርጉት ጨዋታ ትኩረትን ስቧል።
ብሔራዊ ቡድኖቹ በውድድር እና ወዳጅነት ጨዋታዎች በአጠቃላይ 14 ጊዜ ተገናኝተው እንግሊዝ ስድስት ጊዜ ድል ሲቀናት አርጀንቲና በሶስቱ ጨዋታዎች አሸንፋለች። በቀሪ አምስት ጨዋታዎች ላይ አቻ ተለያይተዋል።
በ14ቱ ጨዋታዎች ላይ እንግሊዝ 21 ጎሎችን ከመረብ ላይ ስታሳርፍ አርጀንቲና 15 ግቦችን አስቆጥራለች።
እንግሊዝ የዓለም ዋንጫን አንድ ጊዜ ስታነሳ አርጀንቲና የሶስት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ናት።
በዘንድሮው ዓለም ዋንጫ በተመሳሳይ ስድስት ግቦችን ያስቆጠሩት ሃሪ ኬን እና ጁድ ቤሊንግሃም በዛሬው ጨዋታ የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው።
የ39 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ በጨዋታው ትኩረትን ያገኘ ተጫዋች ነው። በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ስምንት ግቦችን በማስቆጠር ለኮከብ ግብ አግቢነት እየተፎካከረ ይገኛል።
ሜሲ በአጠቃላይ በዓለም ዋንጫ 21 ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው።
የአማካይ ተጫዋቹ ሮድሪጎ ዲ ፖል ከአርጀንቲና በኩል በጨዋታው ልዩነት ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
አርጀንቲና በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ በርካታ ግቦችን (17) ያስቆጠረች ሀገር ናት።
እንግሊዝ ለሁለተኛ ጊዜ፣ አርጀንቲና ለሰባተኛ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ለማለፍ ይፋለማሉ።
ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
አሸናፊው ሀገር ከስፔን ጋር በፍጻሜው ይገናኛል።
ትናንት በተደረገው የመጀመሪያ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ስፔን ፈረንሳይን 2 ለ 0 በመርታት የፍጻሜው ተፋላሚ ሆናለች።