ስፔን ፈረንሳይን በመርታት ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ አለፈች - ኢዜአ አማርኛ
ስፔን ፈረንሳይን በመርታት ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ አለፈች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ተጠባቂ የግማሽ ፍጻሜ መርሐ ግብር ስፔን ፈረንሳይን 2 ለ 0 አሸንፋለች።
ማምሻውን በዳላስ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ማይክል ኦያርዛባል በ22ኛው ደቂቃ የመጀመሪያውን ጎል በፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሯል።
ፍጹም ቅጣት ምቱ የተገኘው የፈረንሳዩ ተከላካይ ሉካ ዲኝ በላሚን ያማል ላይ በሰራው ጥፋት ነው።
የ29 ዓመቱ አጥቂ ኦያርዛባል በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት አምስት አድርሷል።
ፔድሮ ፖሮ በ58ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
በጨዋታው ስፔን በኳስ ቁጥጥር እና የግብ እድሎችን በመፍጠር አንጻራዊ ብልጫ ነበራት።
የፈረንሳይ የአጥቂ መስመር ክፍል በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ያሳየውን አስፈሪነት በዛሬው ጨዋታ መድገም አልቻለም።
በአጠቃላይ ፈረንሳይ በሚጠበቀው የብቃት ደረጃ ላይ አልነበረችም።
የ25 ዓመቱ የፈረንሳይ ተከላካይ ዊሊያም ሳሊባ በ30ኛው ደቂቃ በጉዳት ምክንያት ተቀይሮ ወጥቷል።
ውጤቱን ተከትሎ ስፔን ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ አልፋለች።
ስፔን ከ19ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ የፍጻሜውን ትኬት ቆርጣለች።
የአንድ ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ስፔን በዘንድሮው ውድድር ምንም ሽንፈት ያላስተናገደች ሀገር ሆናለች።
በዘንድሮው የዓለም ዋንጫም የተቆጠረባት አንድ ግብ ብቻ ነው።
ስፔን በፍጻሜው ከእንግሊዝ እና አርጀንቲና አሸናፊ ጋር ትጫወታለች።
ለዋንጫው የተጠበቀችው ፈረንሳይ ለፍጻሜ መብቃት አልቻለችም። በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ሽንፈቷን አስተናግዳለች።
የሁለት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ፈረንሳይ ለአምስተኛ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ የማለፍ ህልሟ ሳይሳካ ቀርቷል።
ፈረንሳይ ከእንግሊዝ እና አርጀንቲና ተሸናፊ ጋር ሶስተኛ ደረጃን ለማግኘት ትጫወታለች።
በዓለም ዋንጫው ስምንት ጎሎችን ያስቆጠረው ኪሊያን እምባፔ ለሁለት ተከታታይ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ የማለፍ ህልሙ ሳይሳካ ቀርቷል።
እምባፔ አሁንም ለከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱ መፎካከሩን ይቀጥላል።
የ27 ዓመቱ አጥቂ 21ኛ የዓለም ዋንጫ በማድረግ ለፈረንሳይ በውድድሩ ላይ በርካታ ጨዋታዎችን ያደረገ ተጫዋች ሆኗል። በነዚህ ጨዋታዎች ላይ 20 ግቦችን አስቆጥሯል።
ሁለተኛው የግማሽ ፍጻሜ መርሐ ግብር ነገ በእንግሊዝ እና አርጀንቲና መካከል ይደረጋል።