ነገ የሚጀመረው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ጠንካራ አንድነትና ዘላቂ ሰላም እንደሚፈጥር ትልቅ ተስፋ አለን -የአዲስ አበባ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ነገ የሚጀመረው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ጠንካራ አንድነትና ዘላቂ ሰላም እንደሚፈጥር ትልቅ ተስፋ አለን -የአዲስ አበባ ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2018(ኢዜአ)፦በነገው ዕለት የሚጀመረው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ጠንካራ አንድነትና ዘላቂ ሰላም እንደሚፈጥር ትልቅ ተስፋ አለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በለያቸው ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ የሚመክረው ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከነገ ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ይካሄዳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ነገ የሚጀመረው ታሪካዊ ምክክር ፍቱን የፖለቲካ መድረክ ብቻ ሳይሆን፣ የእኛን እና የመጪውን ትውልድ እጣ ፈንታና የወደፊት ተስፋ ሙሉ በሙሉ የሚወስን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ጭምር ነው ብለዋል።
በሰለጠነ ንግግር፣ በሰላማዊ ውይይትና ሀገራዊ መግባባት የገጠሙንን ፈተናዎች በሙሉ አልፈን ወደ ብልፅግና በጋራ እንሻገራለንም ነው ያሉት።
የምክክር ጉባኤውን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ በጉባኤው ለሀገር የሚበጁ አጀንዳዎች ላይ መግባባት እንደሚፈጠር ሙሉ እምነት አላቸው።
አቶ አለሙ ካሳ፤ በዚህ ታሪካዊ የምክክር መድረክ ለሀገር የማይበጁ የልዩነት አጀንዳዎች በመደማመጥና በሰከነ ምክክር ተወግደው፣ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንደሚፈጠር ተስፋቸውን ገልጸዋል።
የምክክሩ ስኬታማነት የሀገርን ዘላቂና ጠንካራ አንድነት በመፍጠር በልማት የላቀ ውጤት ለማምጣት እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነው ወጣት ሞገስ ግርማ በበኩሉ፤ በአንዳንድ መሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ አለመግባባቶች ነገ በሚጀመረው የምክክር ጉባኤ መግባባት ላይ ይደረስባቸዋል የሚል ጽኑ እምነት እንዳለው ገልጿል።
ይህ መድረክ ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ የምናበለጽግበትን ዘላቂ ሰላምና ምቹ ምህዳር ለመፍጠር ትልቅ ዕድል ነው ሲል አስረድቷል።
እድገትና ሀገራዊ ብልፅግና የሚረጋገጠው መግባባትና ሰላም ሲኖር ብቻ መሆኑን ያስገነዘቡት ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ጥሩወርቅ ነጋሽ፥ ማናቸውም ችግሮች በጠረጴዛ ዙሪያ በመግባባት መፈታት አለባቸው ብለዋል።
ወይዘሮ መንበረ ዘውዴ በበኩላቸው፤ በአንድነት መቆም የዘላቂ ሰላምና የልማት ጠንካራ መሠረት መሆኑን ተናግረዋል።
ነገ የሚጀመረው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በኢትዮጵያውያን መካከል ፍቅርና አብሮነትን የሚያጠናክር እንደሚሆን ሙሉ ተስፋ እንዳላቸውም ነው የገለጹት።
አክለውም ከአያት ቅድመ አያቶቻችን የተረከብናትን ሀገር ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት፣ የበለጸገችና ምቹ በማድረግ ለልጆቻችን ለማስረከብ በምክክሩ መፍትሔ ማምጣት አለብን ብለዋል።
ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪካዊና ማኅበራዊ የትስስር እሴት እንዳላት ያነሱት አቶ ሰርጸ ከተማ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያውያን የግጭት አዙሪትን የሚያስወግድና መልካም እሴት የሚያጠናክር አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር መመካከር የግድ ያስፈልገናል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ነገ የሚጀመረው የምክክር ጉባኤ መመቻቸቱ ታሪካዊ ዕድል መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህም አብሮ የመኖር እሴትን ለማጽናትና ለማስቀጠል ትልቅ ተስፋ የሰጠ እርምጃ መሆኑን አመልክተዋል።
እርሳቸውን ጨምሮ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነገ የሚጀመረውን የምክክር ጉባኤ በከፍተኛ ጉጉት እንደሚጠብቀው የገለጹት አቶ ከበደ ሎዶሞ በበኩላቸው፤ ከምክክሩ የምናተርፈው ሰላማችንንና አንድነታችንን ማስጠበቅ ነው ብለዋል።
ለምክክሩ መሳካት ገንቢ ሚና በመጫወት መትጋት እንደሚገባም ተናግረዋል።