ቀጥታ፡

ሴቶች ለዘላቂ ሠላም ግንባታና ሁሉን አቀፍ ብልፅግና መሳካት የማይተካ ሚና እየተጫወቱ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2018 (ኢዜአ)፦ሴቶች ለዘላቂ ሠላም ግንባታና ሁሉን አቀፍ ብልፅግና መሳካት የማይተካ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታና የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አየለች እሸቴ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ከዓለም አቀፍ የሴቶች የሰላም ቡድን እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር “ሰላምና ዘላቂ ማህበራዊ አንድነትን ማጠናከር” በሚል መሪ ሀሳብ የልምድ ልውውጥና የትብብር መድረክ አካሂደዋል። 


 

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታና የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አየለች እሸቴ፤ ሴቶች የሀገርን ሰላም እና ብልፅግና በማረጋገጥ ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። 

ፌዴሬሽኑ ሴቶች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ዘርፎች ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ይህም ሴቶች ሀገራዊ የዘላቂ ሰላም ግንባታና ሁሉን አቀፍ ብልፅግናን የማሳካት ጉዞን ይበልጥ ስኬታማ  በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ እያስቻለ ነው ብለዋል። 

ፌዴሬሽኑ ከዓለም አቀፍ የሴቶች የሰላም ቡድን እና አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በሴቶች የአመራር ብቃት ማጎልበት እና በሰላም ግንባታ ረገድ በቅርበት መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የዓለም አቀፍ የሴቶች የሰላም ቡድን የቀጣና -2 ዳይሬክተር ሱ የን ሊ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ሴቶችን ያሳተፉ ሀገር በቀል የሰላም ግንባታ ጥረቶች የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የሰላም ቡድኑ ኢትዮጵያ ሀገር በቀል አቅሞችን በመጠቀም ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት በጎ ሚና ለመጫወት በአጋርነት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

ዘላቂ ሰላም በአንድ ተቋም ወይም በአንድ ግለሰብ ጥረት ብቻ ሊመጣ እንደማይችል በመግለጽ፤ የመንግሥት፣ የትምህርት ተቋማት፣ የሴቶች፣ የወጣቶችና የመገናኛ ብዙኃን ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም