ቀጥታ፡

የገጠር ኮሪደር እና ትራንስፎርሜሽንን ለማፋጠን የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ማስፋፋት ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2018(ኢዜአ)፦የገጠር ኮሪደር ልማትና ትራንስፎርሜሽንን ለማፋጠን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን የማረጋገጥ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

የገጠር ትራንስፎርሜሽን በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል ሁለንተናዊ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል።

የገጠር ሽግግሩ ዋና ዓላማ አርሶ አደሩ ለገዛ ፍጆታው ብቻ ከሚያመርትበት ባህላዊ አሠራር ወጥቶ ለገበያ የሚተርፍ ምርት እንዲያመርት ማድረግና ተረጂነትን በዘላቂነት ማስወገድ ነው።

የተቀናጀ የገጠር መሠረተ ልማቶችን ማስፋትና አገልግሎቶችን ማዳረስ ከስትራቴጂው ዋነኛ ትኩረቶች መካከል አንዱ ነው።


 

የገጠር ኮሪደር ልማትም የእያንዳንዱን አርሶ አደር የመኖሪያ ቤትና የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር በቤተሰብ ደረጃ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያለመ ሰው ተኮር ልማት ነው።

ይህ የኮሪደር ልማት የገጠር መንገዶችን ማሻሻል፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን ማዳረስ እንዲሁም ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን መገንባትን ያካተተ ነው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኮሪደር ልማቱ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት በአግባቡ እና በዕቅድ ለመምራት አስችሏል።

ይህም የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታን በማዘመን፣ አስተማማኝና ዘላቂ የኃይል ስርጭት ለገጠር ከተሞች ለማድረስ ትልቅ እገዛ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት 55 በመቶ መድረሱን ጠቁመው፤ የኃይል አቅርቦት ተደራሽነትን ይበልጥ ለማሳደግ በስፋት እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የገጠር ትራንስፎርሜሽንን እውን ለማድረግና የኮሪደር ልማትን ለማሳለጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን የማረጋገጥ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በበኩላቸው፤ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት በገጠር ከተሞች ውስጥ የኢንቨስትመንትና የንግድ ሥራዎችን ለማስፋት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የገጠር ትራንስፎርሜሽንን ለማፋጠን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመቀናጀት እንደሚሠራም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም