ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክር ጠንካራ የጋራ ሀገር መገንባት የሚያስችል የአዲስ ምዕራፍ መክፈቻ ቁልፍ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ያለፉትን ቁርሾዎች በምክክር ፈትቶ ጠንካራ የጋራ ሀገርን መገንባት የሚያስችል የአዲስ ምዕራፍ መክፈቻ ቁልፍ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ስታከናውን የቆየችው የሀገራዊ ምክክር ሂደት አሁን ላይ ወደ መጨረሻና ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግሯል፡፡

ለኢትዮጵያ ሰላምና ለወደፊት ዕድገት ወሳኝ የሆነው ይህ ሀገራዊ ምክክር፣ ኢትዮጵያውያን የተሰጣቸውን ታላቅ ዕድል እንዲጠቀሙ ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በአጀንዳ ማሰባሰብና በተሳታፊዎች ልየታ ላይ ሰፊ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

ኮሚሽኑ ከነገ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሚያካሂደው ዋናው ሀገራዊ ጉባኤ፣ በዝርዝር ለመምከርና ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማስቀመጥ ከሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተወከሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በአዲስ አበባ ይታደማሉ፡፡

በዋናው ጉባኤ ላይ ምክክር የሚካሄድባቸው ስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ይፋ የተደረጉ ሲሆን፤ እነርሱም የሀገር ግንባታ፣ የመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት፣ የፌዴራል ከተሞች (አዲስ አበባና ድሬዳዋ) ጉዳይ፣ የሃይማኖት ጉዳዮች፣ የተቋማት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች፣ እንዲሁም ሙስና፣ መልካም አስተዳደር እና የሰላም ግንባታ ናቸው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካሪ መብራቱ አለሙ (ዶ/ር)፣ ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያውያን የተሰጠ ታላቅ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን የቆዩ ቁርሾዎችንና የማያስማሟቸውን ጉዳዮች ሁሉ በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ንግግር መፍታት እንደሚችሉና ምንም የሚደብቁት ነገር እንደሌለ አስረድተዋል።

ሁሉም ወገኖች አጀንዳቸውን አቅርበው ለመከራከር ሂደቱ ክፍት መሆኑን ጠቅሰው፤ ሁሉም ወገን ይህንን ታላቅ የሰላም ዕድል በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር እንዳለ ንጉሴ፤ ሀገራዊ ምክክሩ ከጥይትና ከማንኛውም መሳሪያ በላይ ትልቅ ፋይዳና ጉልበት ያለው ሂደት መሆኑን አስረድተዋል።

በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎችና በመዲናዋ አዲስ አበባ ሲካሄዱ የቆዩት የቅድመ ዝግጅት ውይይቶች የፈጠሩት መቀራረብ ቀላል የማይባል ውጤት እና ታላቅ ብርታት ነው ብለዋል።

ውስብስብ ችግሮችን መፍታት የሚቻለው በምክክር ብቻ እንደሆነ አስረድተው፤ የምክክር ሂደቱ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠውና ወሳኝ መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ጉዳዩ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ አጀንዳና የየግል ኃላፊነት እንደሆነ በመግለጽ፤ ይህ በብዙ ዓመታት ጥረት የተገኘ ታላቅ ዕድል በመሆኑ ሁሉም ወገን በውል ተረድቶት እንዲጠቀምም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም