ሕዝብን ያሳተፈና በቴክኖሎጂ የታገዘ የወንጀል መከላከል ሥራ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
ሕዝብን ያሳተፈና በቴክኖሎጂ የታገዘ የወንጀል መከላከል ሥራ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ሕዝብን ያሳተፈና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የወንጀል መከላከል ሥራ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ፖሊስ በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ቀዳሚና ተመራጭ የፖሊስ ተቋም ለመሆን ራዕይ ሰንቆ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋሙ ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ የወንጀል መከላከል ሥራዎችን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ይህም በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍንና ዜጎች የደኅንነት ሥጋት እንዳይኖርባቸው ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አመልክተዋል።
ተቋሙ ራሱን ሪፎርም በማድረግ በአሁኑ ወቅት የሰው ኃይል አቅሙን እያሳደገ መሆኑንና ቴክኖሎጂ የመጠቀም ባህሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቁመዋል።
የቴክኖሎጂ ሽግግሮችን በማጠናከር፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊና ዘመናዊ የፖሊስ አገልግሎትን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
ይህ አቅም በመላው ሀገሪቱ ባሉ የፖሊስ ተቋማት ላይ እያደገ መምጣቱንም ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ጨምረው ተናግረዋል።
የሰላም ግንባታ ሥራ ያለ ኅብረተሰቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ስኬታማ ሊሆን እንደማይችል ጠቁመው፤ በወንጀል መከላከል ዘርፍ የሕዝብ ተሳትፎን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎች በስፋት እየተተገበሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ፖሊስ ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከልና የተፈጸሙ ወንጀሎችን በፍጥነት ለመመርመር ዲጂታል አማራጮችን በስፋት እየተጠቀመ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ኅብረተሰቡ በአካባቢው የሚመለከታቸውን አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችና የወንጀል ድርጊቶች በፍጥነት ለፖሊስ ሪፖርት ማድረስ የሚችልባቸው የዲጂታል መተግበሪያዎችና የስልክ መስመሮች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም አንስተዋል።
በአካል የፖሊስ አባል ሳይኖር ኅብረተሰቡ ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የታገዘ የፖሊስ አገልግሎት የሚያገኝበት ሰው አልባ ስማርት የፖሊስ ጣቢያ መጀመሩንም ገልጸዋል።
ይህ ሰው አልባ የፖሊስ አገልግሎት ዜጎች የደረሰባቸውን ወይም የተመለከቱትን ወንጀል በጣቢያው ውስጥ ባሉ ስክሪኖችና የድምፅ መቅረጫዎች አማካኝነት ለፖሊስ ተቋም ሪፖርት የሚያደርጉበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ቴክኖሎጂው ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ የወንጀል ምጣኔ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱንም ነው ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ የተናገሩት።