ነገ የሚጀመረውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት ለማካሄድ የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ነገ የሚጀመረውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት ለማካሄድ የተሟላ ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 7/2018 (ኢዜአ)፦ነገ የሚጀመረውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት ለማካሄድ አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ፡፡
በሀገራዊ ምክክሩ ዋና ጉባኤ ዋዜማ ከኮሚሽኑ ግቢ ጀምሮ የማርቺንግ ባንድ ትርዒት እየቀረበ ይገኛል።
ማርቺንግ ባንዱ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር የተለያዩ ትርዒቶችን እያቀረበ ይገኛል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ነገ ለምትጀምረው ሀገራዊ ጉባኤ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናቀው ዋዜማው ላይ ደርሷል።
ነገ በሚጀመረው በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ላይ ከአራት ሺህ በላይ ዜጎች በጋራ በመቀመጥ በሀገራቸው የጋራ ጉዳዮች ላይ በሰፊው ይመክራሉ ብለዋል።
ሀገርን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት በሚደረገው በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ላይ እያንዳንዱ ተመካካሪ በንቃት እንዲመካከር ጥሪ አቅርበዋል።
ኮሚሽኑ ከነገ ሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሚያካሂደው ዋናው ሀገራዊ ጉባኤ፣ በዝርዝር ለመምከርና ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማስቀመጥ ከሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተወከሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል።