ቀጥታ፡

በትምህርት ቤቶች ምቹ የመማሪያ አካባቢ ለመፍጠርና ገቢ ለማመንጨት የተጀመሩ የችግኝ ተከላ ሥራዎች ይጠናከራሉ

ወላይታ ሶዶ፤ ሐምሌ 7/2018 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በትምህርት ቤቶች ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው ችግኞችን በመትከል ምቹ የመማሪያ አካባቢና ገቢ ለመፍጠር የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ ሲሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ በሚገኘው ሳዝጋ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቅጥር ግቢ ውስጥ "ተስፋን እንትከል፤ አረንጓዴ መሬት ለልጆቻችን እናውርስ!'' በሚል መሪ ሃሳብ ችግኝ ተክለዋል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት፤ በትምህርት ተቋማት የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች በመትከል ምቹ የመማሪያ ከባቢን የመፍጠርና የውስጥ ገቢን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

ችግኞቹ የአካባቢ መራቆትን ከመከላከል ባለፈ ለትምህርት ቤቶች ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙ የፍራፍሬ፣ የቡና፣ የእንሰት እና ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ችግኞችን በመትከልና ቀድሞ የተተከሉትን በመንከባከብ ለኑሮና ለመማሪያ ምቹ የሆነ አረንጓዴ አካባቢን ለትውልድ ለማውረስ የተጀመረው ሥራ እንደሚጠናከርም ገልጸዋል።

የጎፋ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሞገስ መኩሪያ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በዞኑ ባሉ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የፍራፍሬ እና የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል በንቅናቄ እየተሰራ ነው።


 

በችግኝ ተከላው ሁሉም የትምህርት ማህበረሰብ እየተሳተፈ መሆኑን ጠቁመው፣ ተግባሩ ምቹ የመማሪያ አካባቢ ለመፍጠር እና የትምህርት ቤቶችን የውስጥ ገቢ ለማሳደግ አስተዋጽኦው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በተያዘው ክረምትም በዞኑ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የፍራፍሬ፣ የቡና እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን አስረድተዋል።


 

በችግኝ ተከላ መርሀግብሩ ላይ ከተሳተፉት የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች መካከል የአራተኛ ክፍል ተማሪ ልኡል ወንዱ እና የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ናርዶስ ኢዮብ፤ ችግኝ መትከል ያለውን ጥቅም አውቀው በትምህርት ቤታቸው በመትከላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።


 

ችግኝ መትከል ንጹህ አየር እንድንተነፍስ እና ውብ አካባቢ እንዲኖረን ስለሚያደርግ የተከልነውን ችግኝ ተንከባክበን የማሳደግ ኃላፊነታችንን እንወጣለን ሲሉም ተናግረዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ የ2018 ዓ.ም የክረምት ወራት የትምህርት ንቅናቄ ትናንት በሳውላ ከተማ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም