ቀጥታ፡

በከተማ አስተዳደሩ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ236 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ይሆናሉ

ባህር ዳር ፤ ሐምሌ 7/2018 (ኢዜአ)፡- በበከተማ አስተዳደሩ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ236 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን  የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ  ገለጸ፡፡

የመምሪያው ኃላፊ ወይዘሮ ሰብለ ዘውዱ ለኢዜአ እንደገለጹት፣በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት  236 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው፡፡ 

በዚሁ ወቅት 418 ቤቶችን የማደስና በአዲስ መልክ የመገንባት እቅድ ተይዞ  ወደ ስራ የተገባ ሲሆን የአቅመ ደካሞችን መሬት በሰብል የመሸፈን ስራም ይከናወናል ነው ያሉት።

በተጨማሪም የማጠናከሪያ ትምህርት የመስጠት፣ ችግኝ የመትከል፣ ደም በመለገስና ሌሎች የልማት ስራዎችም  በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ  እንደሚከናወኑ ነው የገለጹት።


 

በአጠቃላይ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ስራዎች የሚከናወኑ ሲሆን  234 ሺህ 600 በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ይሳተፋሉ ብለዋል።

እስካሁን በተደረገ ጥረትም ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የበጎ ፈቃድ ስራዎችን ማከናወን መቻሉን አስረድተዋል።

እስከ መጪው የነሐሴ ወር መጨረሻ  በሚቀጥለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የከተማው ነዋሪና ባለሀብቱ በገንዘቡ፣ በእውቀቱና በጉልበቱ የድርሻውን እንዲያበረክትም ጠይቀዋል።

የበጎ ፈቃድ ስራው  ተሳታፊ የሆኑት ወጣት አዳነ ተዘራ እና ቻሌ ካሳሁን ፤ሰውን መርዳት ወደር የለሽ የህሊና እርካታና ደስታን የሚሰጥ በመሆኑ ወጣቱ ተሳትፎውን ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።


 

የፈረሱ የአቅመ ደካማ ዜጎችን ቤት በመጠገንና በአዲስ መልክ በመገንባትም ከአስቸጋሪ ህይወት እንዲላቀቁ ለማድረግ  እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በባህርዳር ከተማ  ከ50 ዓመታት በላይ የኖሩት እማሆይ እናንየ ታመነ፤ በእርጅና ምክንያት ቤታቸው በመፍረሱ በክረምትና በበጋ የተለያየ ችግር ይደርስባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።


 

በአሁኑ ወቅት በበጎ ፈቃደኞች ቤታቸው በአዲስ መልክ ተገንብቶ የተስተካከለ ሲሆን ተጨማሪ የቤት እቃም እንደተሟላላቸው ተናግረዋል።

 በተደረገላቸው ድጋፍ ከነበሩበት አስከፊ ኑሮ ወጥተው ቀሪ ጊዜያቸውን በደስታ ለማሳለፍ እንዳስቻላቸው በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም