ቀጥታ፡

መንግሥት የሎጂስቲክስ ዘርፉን በማዘመን የገቢና የወጪ ንግድን ቀልጣፋ በማድረግ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2018 (ኢዜአ)፦ መንግሥት የኢትዮጵያን የሎጂስቲክስ ዘርፍ በማዘመን የገቢና የወጪ ንግድን ቀልጣፋ በማድረግ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የዕቃ አስተላላፊዎች እና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር (EFFSAA)፣ ከተለያዩ የመንግሥት፣ የግል እና ዓለም አቀፍ ተቋማት የተውጣጡ የሎጂስቲክስ ባለሙያዎችን በዓለም አቀፍ ዕውቅና ባለው የፊያታ (FIATA) ዲፕሎማ አሰልጥኖ አስመርቋል፡፡ 

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ፤ የአገሪቱን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ዘርፉ የማይተካ ሚና እንዳለው አስታውሰዋል። 

መንግሥት የወጪና የገቢ ምርቶችን በሚፈለገው ፍጥነትና ጥራት ለማሳለጥ የሎጂስቲክስ ዘርፉን በሰለጠነ የሰው ኃይል ለማጠናከርና ለማዘመን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ለዚህም የዛሬዎቹ ተመራቂዎች የዘርፉን አቅም በመገንባት፣ በአቅርቦት ሰንሰለት ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን በብቃት በመፍታትና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን በመዘርጋት  የሎጂስቲክስ ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር አገራዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍራኦል ጣፋ በበኩላቸው፣ ዘርፉን ለማዘመንና ወቅቱን የዋጀ አሠራር ለመዘርጋት የሚያስችል የአሥር ዓመት ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ተግባር መገባቱን ይፋ አድርገዋል። 

የዘርፉን ትራንስፎርሜሽን ለማሳካትም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ የዕቃ አስተላላፊዎች እና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዳዊት ውብሸት (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ስልጠናው በአገሪቱ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍ ፋይዳው ከፍተኛ ነው። 

ማኅበሩ የአቅም ግንባታ በመፍጠርና ምርምርን በማካሄድ ዘርፉን ለማዘመን ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የዘርፉን ተወዳዳሪነት በማሳደግና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲዘረጋ በማድረግ ረገድም የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም