የኢትዮጵያ ማኛ ወርቅ፤ ከተንጣለለው የጎጃም ማሳ ወደ ዓለም ገበያ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ማኛ ወርቅ፤ ከተንጣለለው የጎጃም ማሳ ወደ ዓለም ገበያ
በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞኑ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የጤፍ ምርት ከሚገኝባቸው አካባቢዎች መካከል ይጠቀሳል። ለዚህ ስኬት የተፈጥሮ ጸጋው ብቻ ሳይሆን የአርሶ አደሮች ትብብር፣ ዘመናዊ የእርሻ አሰራርና የገበያ ትስስር መጠናከር ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል።
የተንጣለለው የምስራቅ ጎጃም ማሳ በጤፍ ተሸፍኖ ማየት ስሜትን ይገዛል። በማሳው መካከል ደግሞ አርሶ አደሮች በጋራ እየሰሩ መመልከት ከትውልድ ትውልድ የተላለፈ የመረዳዳትና ለሺህ ዘመናት ለዘለቀ አስተራረስ አብነት ነው።
የጎጃም ጤፍ በጥራቱ ቢታወቅም፣ ምርቱን በተሻለ ዋጋ ለመሸጥ የሚያስችል የገበያ ትስስር ውስን ነበር።
አርሶ አደሩ በብዙ ድካም ያመረተውን ምርት ለደላሎች በዝቅተኛ ዋጋ ለመሸጥ ይገደዳል። በምርቱ ላይ የሚፈጠረው እሴትም እምብዛም ነው።
ዛሬ ግን ያ ታሪክ እየተለወጠ ይመስላል። በደብረ ማርቆስ ከተማ የተቋቋመውና የማኛ ጤፍ ዱቄትን ወደ ዓለም ገበያ መላክ የጀመረው ፋብሪካ የአርሶ አደሩን ምርት በቀጥታ በመቀበል ወደ እሴት የሚቀይር ድልድይ ሆኗል። ከእርሻ ወደ ፋብሪካ፣ ከፋብሪካ ወደ ውጭ ገበያ የሚዘልቀው ይህ የእሴት ሰንሰለት የአርሶ አደሩን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በማሳደግ አዲስ የለውጥ ምዕራፍን ከፍቷል።
የማኛ ጤፍ ዱቄት ማምረቻ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ሰማኸኝ ጌታቸው እንደሚገልጹት፣ ፋብሪካው በቀን በአማካይ ከ600 እስከ 800 ኩንታል ጤፍ የሚፈጭ ሲሆን፥ ሥራ በጀመረባቸው ጥቂት ወራት ውስጥ 600 ቶን እሴት የተጨመረበት ጤፍ ለውጭ ገበያ አቅርቧል።
በዚህም አንድ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለሀገር አስገኝቷል። ይህ አሃዝ የጤፍ ምርት በፋብሪካ እሴት ሲጨምር የሚፈጠረውን የኢኮኖሚ ጥቅም በግልጽ ያሳያል ብለዋል።
ከዚህ በላይ ደግሞ ፋብሪካው ለ70 የሚጠጉ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩ የግብርና ልማት ከኢንዱስትሪ ጋር ሲሰናሰል የሚፈጠረውን ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያመለክታል።
ይህ ማለት አንድ የጤፍ ሰብል ከማሳ እስከ ውጭ ገበያ ድረስ በሚያደርገው ጉዞ በርካታ የሥራ ዕድሎችን፣ የገቢ ምንጮችንና የኢኮኖሚ እሴቶችን ይፈጥራል ማለት ነው።
በምስራቅ ጎጃም ዞን ትርፍ አምራች ከሆኑ አካባቢዎች መካከል በደጀን ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮችም ይህንን ለውጥ በቀጥታ እየተጠቀሙበት ነው። በክላስተር ማረስ የምርት ጥራትን በማሻሻል ጉልህ ጠቀሜታ ያስገኛል።
ኢዜአ ከዚህ ቀደም በወረዳው በኩታ ገጠም የጤፍ ምርት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን በጎበኘበት ወቅት የተመለከተው እውነትም ይህንኑ ነው። ፋብሪካው ደግሞ ከተጠቃሚነት ላይ ተደማሪ ጠቀሜታ የሚያገኙበትን ዕድል ፈጥሯል።
በደጀን ወረዳ በክላስተር ተደራጅተው ጤፍን በስፋትና በጥራት ከሚያመርቱ አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር መኩሪያው ታደለ አንዱ ሲሆኑ፤ የኩታ ገጠም እርሻ የጉልበት ወጪን በመቀነስ የምርት ጥራትና ብዛትን በማሳደግ ከፍተኛ ውጤት እንደሚያስገኝ ይገልፃሉ።
በክላስተር ማምረት በአንድ ጊዜ መዝራት፣ መከታተልና መሰብሰብ በመቻሉ የምርት ብክነትን መቀነስ እንደተቻለም ሌላው አርሶ አደር ሸጋው ከፍያለው ያብራራሉ።
እንደ እርሳቸው ገለጻም፤ አርሶ አደሮች በአንድነት መስራታቸው የግብርና ሥራዎችን በወቅቱ ለማከናወን አስችሏል። ይህም በምርታማነት ላይ ቀጥተኛ አወንታዊ ተፅዕኖን ፈጥሯል።
በተመሳሳይ አቶ ውዱ ሞሱ እንደሚሉት፤ የአርሶ አደሮች መተባበር ከዘር እስከ ምርት አሰባሰብ ድረስ በሁሉም ሂደት ውጤታማ አድርጓቸዋል። ምርቱ ሲደርስም በደቦ በመሆን በአጭር ጊዜ በመሰብሰብ የጊዜና የጉልበት ብክነትን አስቀርቷል።
የአርሶ አደሩ ስኬትም በማሳ ብቻ የሚቆም አይደለም። ከምርቱ መገኛ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ደብረ ማርቆስ ከተማ የተቋቋመው የማኛ ጤፍ ዱቄት ማምረቻ ፋብሪካ ሥራ መጀመሩ የደጀንና የአካባቢውን አርሶ አደሮች ከማሳ በቀጥታ ወደ ዓለም ገበያ የሚያገናኝ አዲስ የእሴት ሰንሰለት ፈጥሯል። ከዚህ ቀደም ጤፍ እንደ ጥሬ ምርት ብቻ ይሸጥ የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ግን በፋብሪካ ተበጥሮ፣ ተፈጭቶ፣ በዘመናዊ መልክ ታሽጎ እሴት ተጨምሮ ወደ ውጭ ገበያ እየተላከ ነው።
የደብረ ማርቆስ ከተማም በዚህ ሂደት የኢንዱስትሪ ማዕከል እየሆነች ነው። በከተማዋ የሚገኙ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የአካባቢውን ጥሬ እቃ በመጠቀም እሴት የሚጨምሩ በመሆናቸው ግብርናን ከኢንዱስትሪ ጋር የሚያስተሳስሩ የልማት ሞዴሎች እየሆኑ መጥተዋል። ይህም ለጎጃም ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያ የግብርና ሽግግር አቅጣጫን የሚያሳይ ጠቃሚ ልምድ ነው።
የኢትዮጵያ ጤፍ በባህላችን ያለውን ክብር ተጠብቆ በዓለም ገበያም ተፈላጊነቱን እያሳደገ ነው። ይህን ዕድል በተሻለ መንገድ ለመጠቀም የምርት ጥራትን ማሻሻል፣ የማቀነባበር አቅምን ማስፋት፣ የአርሶ አደሩን የገበያ ትስስር ማጠናከርና ተመሳሳይ የእሴት ጭማሪ ኢንዱስትሪዎችን በሌሎች አምራች አካባቢዎች ማስፋፋት ቀጣዩ የልማት ምዕራፍ ይሆናል።
ከጎጃም የተንጣለለ የእርሻ ማሳ የሚነሳው የጤፍ እህል ዛሬ በፋብሪካ እሴት ተጨምሮ ወደ ዓለም ገበያ እየተጓዘ ነው፤ ይህም የኢትዮጵያ ግብርና ከባህላዊ አመራረት ወደ እሴት ጭማሪ ኢኮኖሚ እየተሸጋገረ መሆኑን የሚያሳይ ተጨባጭ ውጤት ሆኗል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ተመስገን ተድላ፣ ከተማዋ ለኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ተመራጭ እየሆነች የመጣችው በቂ ጥሬ ዕቃ፣ የሰው ኃይል፣ የተሻለ የመጓጓዣ አገልግሎትና የሰላም ሁኔታ በመኖሩ መሆኑን ያብራራሉ። በተለይም የጎጃም አካባቢ የግብርና ሃብት ለእሴት ጨማሪ ኢንዱስትሪዎች ጠንካራ መሠረት እየፈጠረ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
በለውጡ ዓመታት 253 የአምራች ኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባታቸውና አብዛኞቹ ወደ ምርት መሸጋገራቸው የአካባቢው ኢኮኖሚ እያደገ መምጣቱን ያሳያል። ከእነዚህ መካከል የጤፍ ማቀነባበሪያ ፋብሪካው የጎጃም ማኛ ወርቅ የሆነውን የጤፍ ምርት እሴት ጨምሮ ወደ ዓለም ገበያ በማቅረብ ለአርሶ አደሩ፣ ለከተማዋና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ተጨባጭ ጥቅም የሚያስገኝበትን አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል ይላሉ።
በዚህ መልኩ በምስራቅ ጎጃም ዞን ያለውን ሰፊ የጤፍ ምርት በደብረ ማርቆሱ ፋብሪካ እሴት ተጨምሮ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ገበያ መድረሱ የኢትዮጵያ ግብርና ከጥሬ ምርት ሽያጭ ወደ እሴት ጭማሪ፣ ከአካባቢ ገበያ ወደ ዓለም ገበያ እየተሸጋገረ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። ይህም ጤፍ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያጠናክር ስትራቴጂያዊ ሀብት መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን አብራርተዋል።