በምክክር መፍትሄ በመሻት ከግጭት አዙሪት መውጣት እና ለዜጎቿ ሁሉ የምትመች ሀገር መገንባት አለብን- የአዲሃን ሊቀመንበር - ኢዜአ አማርኛ
በምክክር መፍትሄ በመሻት ከግጭት አዙሪት መውጣት እና ለዜጎቿ ሁሉ የምትመች ሀገር መገንባት አለብን- የአዲሃን ሊቀመንበር
ባህር ዳር፤ ሐምሌ 7/2018 (ኢዜአ)፡- በምክክር መፍትሄ በመሻት ከግጭት አዙሪት መውጣት እና ለዜጎቿ ሁሉ የምትመች ጠንካራ ሀገር በጋራ መገንባት አለብን ሲሉ የአማራ ዲሞክራሲ ሃይሎች ንቅናቄ (አዲሃን) ሊቀመንበር ተስፋሁን አለምነህ ገለጹ።
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም፣ በሀገራዊ አንድነትና በሰላም ግንባታ ዙሪያ አዲሃን የማይናወጥ አቋም በመያዝ የሚሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በርካታ ሂደቶችን አልፎ የምክክር ጉባኤው የሚካሄድበት ዋዜማ ላይ የሚገኝ ሲሆን በነገው እለትም በአዲስ አበባ መካሄድ የሚጀምር ይሆናል።
በምክክሩና አጠቃላይ የፖለቲካ እንቅስቃሴውን በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአማራ ዲሞክራሲ ሃይሎች ንቅናቄ (አዲሃን) ሊቀመንበር ተስፋሁን አለምነህ፤ የምክክሩ ሂደት እስካሁን በጥሩ ስኬት መዝለቁን አንስተው የመጨረሻው ውጤትም የተሳካ እንዲሆን የሁላችንም ዝግጁነትና ቀና ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የግጭትና ጦርነት መዘዝ ብዙ ዋጋ ያስከፈለ መሆኑን የተመለከትነው በመሆኑ ከምንም በላይ ለዘላቂ ሰላምና ለሀገር ልማት በጋራ ቆመን የምንሰራበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል።
የምክክር ሂደቱ በኢትዮጰያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘ እድል መሆኑን ያነሱት አቶ ተስፋሁን፤ በተለዩ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት በመምከር ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት መዘጋጀት አለብን ብለዋል።
የፖለቲካ ዓላማን በሃይል ለማሳካት የሚደረግ ጥረት በየትኛውም መመዘኛ የማያዋጣ እና አክሳሪ መሆኑን ገልጸው ለኢትዮጵያ የቆዩ የፖለቲካ ስብራቶች ዘላቂ መፍትሄው ምክክር መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም፣ በሀገራዊ አንድነትና በሰላም ግንባታ ዙሪያ አዲሃን የማይናወጥ አቋም በመያዝ የሚሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በዚህ ምክክርም መፈታት ያለባቸውን አጀንዳዎች ማስያዝ መቻሉን ጠቅሰው፤ ለመፍትሄውም በጋራ መረባረብ ይገባል ነው ያሉት።
ይህ ምክክር እንዳይካሄድ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ፍላጎት ቢኖርም የጠላቶችን ፍላጎት በትብብር በማክሸፍ በምክክሩ የምንፈልገውን ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ ገልፀዋል።
በተለይም ምሁራን የሃገርን ብሄራዊ ጥቅም በማስከበር ረገድ ሚናቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ከትውልድ ግንባታ በተጓዳኝ የምክክርና ውይይት ባህል እንዲዳብር በማድረግ ረገድ በተለይም ምሁራን የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።